ዜና፡- ከ5 ቢሊየን ብር በላይ በሕገ-ወጥ መንገድ በማዘዋወር የተጠረጠረ ግለሰብና ግብረ-አበሮቹ በቁጥጥር ስር ማዋሉን የፌደራል ፖሊስ ገለፀ

አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ጥቅምት 16፣ 2015 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ ከ5 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ በሕገ-ወጥ መንገድ ሲያንቀሳቅስ የነበረ ግለሰብን ከ25 ግብረ-አበሮቹ ጋር በቁጥጥር ሥር አውሎ ምርመራ እያረገ መሆኑን ገልጿል፡፡

በወንጀሉ ተጠርጥሮ በቁጥጥር ስር የዋለው ግለሰብ ሳሙኤል እጓለ አለሙ ፣ በቅፅል ስሙ ሳሚ ዶላር የሚባል ሲሆን ነዋሪነቱን በአዲስ አበባ ከተማ በማድረግ ወደ አሜሪካን ሀገር በተደጋጋሚ ይመላለስ እንደነበር ፖሊስ ገልጿል።

ተጠርጣሪ ግለሰቡ የኤሌክትሪክ መሳሪያዎች፣ የቤት እና የቢሮ እቃዎች እንዲሁም ተዛማጅ መገልገያዎች የችርቻሮ ንግድ ፍቃድን ሽፋን በማድረግ ሕገ-ወጥ የውጭ ምንዛሬና በሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር ወንጀል ተጠርጥሮ በራሱ እና ዮዲት እጓለ ዓለሙ ከተባለች እህቱ ጋር በመሆን በስማቸው በተለያዩ ባንኮች በከፈቷቸው ሃያ አምስት የባንክ አካውንቶች በአንድ ዓመት ውስጥ ከ247 ሚሊየን ብር በላይ ማንቀሳቀሳቸውን ፖሊስ ገልጾ ምርመራ እየተካሄደባቸው መሆኑን ጨምሮ አብራርቷል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ተጠርጣሪ ግለሰቡ ከ25 የወንጀል ግብረ-አበሮቹ ጋር በመሆን በህገ-ወጥ መንገድ ከ5 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ ሲያንቀሳቅሱ እንደነበር በቅድመ ምርመራ እንደተደረሰባቸው የፌዴራል ፖሊስ አሳውቋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ በሕገወጥ የውጭ ሀገር የገንዘብ ዝውውር፣ በግብር ስወራ ወንጀል እና ከህወሃት ጋር የግንኙነት መረብ በመፍጠር ከፍተኛ ገንዘብ ሲያዘዋውሩ እንደነበር ተጠርጥረው ምርመራ እየተካሄደባቸው መሆኑን የፌዴራል ፖሊስ ገልጿል።

ጠቅላይ ምንስትር አቢይ አህመድ ባለፈዉ ሰኞ ባወጡት መግለጫ ህገ ወጥ የውጭ ምንዛሬ ዝዉዉር ሀገሪቷን እያጋጠሟት ካሉ የዕድገት እንቅፋቶች መሀል መሆኑን ጠቅሰው ፈጣን እርምጃ ሊወሰድበት ይገባል ብለዉ ነበር::

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከዚህ ቀደም 391 ሰዎች በሕገወጥ መንገድ ገንዘብ ሲያዘዋውሩ እና የሐዋላ ሥራ ሲያከናውኑ በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በሕግ ተይዟል ማለቱ ይታወሳል:: አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.