ዜና፡- ጁዌሪያ መሀመድ የፖሊስ አባል “ሆነ ብሎ” በተኮሰው ጥይት መገደላቸዉን የሶማሊ ክልል ባለስልጣን አረጋገጡ

ጁዌሪያ መሀመድ የሁለት ልጆች እናት ነበረች ። ፎቶ: ማህበራዊ ሚዲያ


አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 16/2015 ዓ.ም፡- የገዥው ብልፅግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ እና የሶሶማሊ ክልል የፓርላማ አባል ጁዌሪያ መሀመድ አንድ የፖሊስ አባል “ሆነ ብሎ” በተኮሰው ጥይት መገደላቸዉን የክልሉ የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ሀላፊ አቶ መሀመድ ጉራይ ለአዲስ ስታንዳርድ አረጋገጡ።

ጁዌሪያ መሀመድ ጥቅምት 15 ቀን በክልሉ ዋና ከተማ ጅግጅጋ ጋራድ ዊልዋል አየር ማረፊያ ውስጥ በአንድ የፌደራል ፖሊስ አባል በተተኮሰ ጥይት ህይወቷ አልፋል። ድርጊቱ እህቷ አያን መሀመድ እና የክልሉ የካቢኔ አባል አብዲራሺድ መሀመድን ጨምሮ ሌሎች ሶስት ሰዎች ላይ የመቁሰል አደጋ አድርሷል።

አቶ መሐመድ እንዳሉት “በእሱ [በፖሊሱ] እና በፓርላማ አባሏ መካከል የተወሰነ ጭቅጭቅ ነበረ፣ እናም የፖሊስ መኮንኑ በራሱ እርምጃ ወሰደ”። ምርመራው ገና በጅምር ላይ መሆኑን የገለጹት አቶ መሐመድ ግድያው “ፖለቲካዊ” አይደለም ብለዋል።

የፓርላማ አባሏን ህልፈት ተከትሎ ትናንት ጥቅምት 26 በጅግጅጋ በሟች መኖሪያ ቤት 05 እና 06 ቀበሌ አካባቢ የተቃውሞ ሰልፎች መደረጉን የጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ መምህር ሲራጅ አብዲቃድር ለአዲስ ስታንዳርድ ተናግረዋል። ሰልፈኞቹ ለሟቿ ፍትህ እስካልተገኘ ድረስ አስክሬኗ እንዳይቀበር የጠየቁ ሲሆን የክልሉ የጸጥታ ሃይሎች  አስለቃሽ ጭስ መተኮስን ጨምሮ ሌሎች እርምጃዎችን እንደወሰዱ በዚህም አራት ሰዎች ላይ የመቁሰል አደጋ ሲደርስ ሌሎች አስር ሰዎች መታሰራቸዉን ጨምሮ ተናግረዋል።

የክልሉ ምክር ቤት አባል አሲያ አብዲ እና የሻካል ቲቪ ጋዜጠኛ አያንሌ በተቃውሞ ሰልፉ ላይ በተወሰደ እርምጃ በክልሉ ፖሊስ ጉዳት ከደረሰባቸው መካከል ይገኙበታል። የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ኢብራሂም አብዲቃድር እና አብዲ ባሩድ ደግሞ በክልሉ ፖሊስ በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም አክለዋል።

የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ሀላፊዉ አቶ መሐመድ ግን በትላንትናው እለት በተካሄደው የተቃውሞ ሰልፍ ላይ በግለሰቦች ላይ ደረሰ የተባለዉን ጉዳት እና እስራት ከሰልፉ ጋር በተያያዘ ምንም የተፈጠረ ነገር የለም በማለት አስተባብለዋል::
አቶ ሲራጅ እንድሚለዉ የጅግጅጋ ከተማ ዉስጥ ከትላንትናው የተሻለ መረጋጋት ቢኖርም “በተለይ በ05 እና 06 ቀበሌ የተዘጉ መንገዶችና ሱቆች አሉ” ብለዋል።

ጁዌሪያ መሀመድ የሶማሊ ክልል ፓርላማ አባል፣ የብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል እና የኦጋዴን ወልፌር ሶሳይቲ ዋና ስራ አስፈፃሚ እንዲሁም የሁለት ልጆች እናት ነበረች። አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.