ዜና፡ ከቤተ ክርስቲያን ቀኖና ውጭ አዲስ ሲኖዶስ አቋቁመዋል የተባሉት አካላት የተደረሰውን ስምምነት መጣሳቸውን ቤተ ክርስቲያን አስታወቀች

አዲስ አበባ፣ የካቲት 11/2015 ዓ.ም፡- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ህገ ወጥ የኤጴስ ቆጶሳት ሹመት ሰጥተዋል፣ አዲስ ሲኖዶስ አቋቁመዋል ካለቻቸው አካላት ጋር ስምምነት ላይ ብትደርስም ሊቃነ ጳጳሳቱ ስምምነቱን መጣሳቸውን ቅዱስ ሲኖዶስ  አስታወቀ፡፡

“ወደ ዘጠኝ ሰዓት አካባቢ አዲሱ ሲኖዶስ በሚል አዲስ ስም ባስተላለፉት ሁሉም በአንድነት ጵጵስናው የሚመለከታቸውም የማይመለከታቸውም የኤጲስ ቆጶስነቱ ደረጃም በስምምነቱም በጋራ የጠፋ ወይም የተሻረ የተደመሰሰ መሆኑን እያወቁም የቅድስናውን ልብስ በመልበስና ሌሎችም የስምምነቱ አካል ሆነው ስምምነቱን ያነበቡት ሳይቀሩ በአንድ ላይ ስምምነቱን ጥሰውታል ቀኖናውን እንደገና ደግመው ጥሰውታል” በማለት የዱስ ሲኖዶስ ስራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ አብርሃም ትላንት በሰጡት መግለጫ ገልፀዋል።

“ሀይማኖቱንም ሕጉንም መልሰው መላልሰው ጥሰውታል።ሹመታቸው ሕጋዊ እንደሆነና በምንም ይሁን በምን የማይሻር መሆኑንም መልእክት አስተላልፈዋል” ያሉት  አቡነ አብርሃም አክለውም በሃይማኖታዊ መንገድ በሰላምና በፍቅር በክርስቶስ ደም የተመሠረተችውን ቤተ ክርስቲያን ከመጠበቅ በክርስቶስ ደም የተዋጁትን ምእመናን ከማስተማር ይልቅ በኃይልና በጉልበት ሁሉንም በነገረ ሰሪነት ግጭት በመፍጠር ሁሉንም ለመቆጣጠር ከዕለት ወደ ዕለት ደፋ ቀና ሲሉ ይታያሉ ብለዋል፡፡

በሶስቱ ጳጳሳት እና በ25ቱ ኤጴስ ቆጶሳት በኩል ትላንት የተሰጠው መግለጫ እንደሚገልፀው በሶስቱ አባቶች የተሾሙት ኤጲስ ቆጶሳትን አስመልክቶ የተደረሰበትን ስምምነት አጠቃላይ ሀሳቡን እንደሚቀበሉት ጠቅሶ ነገር ግን በሶስቱ ሊቀፓፓሳት የተደረገው ሹመት የዶግማም ሆነ የቀኖና ጥሰት የሌለው ስለሆነ አሁን ሹመቱ መነሳቱ ቀኖና ቤተክስቲያንን ስለሚጥስ እንዲሁም ድጋሚ ይሰጣል መባሉም ዶግማዉን ስለሚጥስ በድጋሚ በጋራ እንዲመከርበት ጥሪ አቅርቧል።

አቡነ አብረሃም በሰጡት መግለጫ “ሀይማኖትን ለመበረዝ ታጥቀው ለመነሳታቸው ከዚህ በላይ ማረጋገጫ የለም፡፡የሰጡት መግለጫ  ቤተክርስቲያኒቱን የማይወክል መሆኑን፣ እነሱ ራሳቸውንም የማይወክል መሆኑን፣ የተገደዱበት ነገር ካለ በግልጽ እስካልተናገሩ ድረስ አቋማቸውን እስካላስተካከሉ ድረስ ከቤተ ክህነት እንዲወጡልንም እንጠይቃለን “ሲሉ ጨምረው ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በውስጧ ተከስቶ የነበረው ችግር በቀኖና ቤተ ክርስቲያን መሠረት መፈታቱን ያሳወቀችው የካቲት 8 ነበር። በስምምነቱ ሦስቱ ሊቃነ ጳጳሳት ብጹዕ አቡነ ሳዊሮስ፣ ብጹዕ አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ፣ብጹዕ አቡነ ዜና ማርቆስ እና በእነሱ የተሾሙት 25 ኤጴስ ቆጶሳት ወደ ቀደመ ሀገረ ስብክታቸውና የክነት ማዕረጋቸው እንዲመለሱ መወሰኑንም ገልጻለች።

በተጨማሪም  በኦሮሚያ ክልል በኦሮምኛ ቋንቋ ትምህርት፤ ቅዳሴ እና ሌሎችም አገልግሎቶች እንዲሰጡ የተጀመረው ሥራ የሕዝቡን ጥያቄ በሚመልስ መልኩ እንዲጠናከር የተወሰነ መሆኑን አስታውቆ ለዚህም ከዚህ በፊት ከተደረገው በተጨማሪ አስፈላጊው በጀትና የሰው ኃይል እንደሚመደብ አመላክቷል። በተጨማሪም በኦሮሚያ እና በሌሎች አካባቢዎች የሚያገለግሉ ቋንቋውን የሚያውቁ አገልጋዮችን የሚያሠለጥኑ ተጨማሪ ኮሌጆች እና ማሠልጠኛዎች እንዲከፈቱ፣ የተከፈቱትም እንዲጠናከሩ እንደሚደረግ ከስምምነት ላይ ደርሰው ነበር።

ዳራ

ጥር 18/ 2015 ዓ.ም ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ከቀኖና እና ከእውቅናዬ ውጭ የሆነ ሕገ ወጥ የኤጲስ ቆጶሳት እና ጳጳሳት ሹመት ተስጥቷል በተባለው ጉዳይ ላይ ቅዱስ ሲኖዶሱ ባካሄደው አስቸኳይ ምልአተ ጉባኤ፣ ሲመቱን በሰጡ ሶስት ሊቀጳጳሳት እና 25 ተሿሚዎች ላይ የውግዘት ውሳኔ ማስተላለፏ ይታወቃል፡፡ የተወገዙት ሶስቱ  ጳጳሳት እና 25 ኤጴስ ቆጶሳት እሁድ ጥር 20 በምላሹ 12 የነባሩን ሶኖዶስ አባላትን በማውገዝ የራሳቸውን ኤጴስ ቆጶሳት በመሾም ወደ ተመደቡበት ሀገረ ስብከት እየተሰማሩም ነበር፡፡

ቤተክርስቲያኗ ለሁለት እንድትከፈል ሊያደርግ የነበረው ክስተት፣  በኦሮምያ ክልል ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን በሶዶ ዳጬ ወረዳ በወሊሶ ከተማ በበአለ ወልድ ቤተ ክርስቲያን በአቡነ ሰውሮስ እና ሌሎች ሁለት ጳጳሳት መሪነት በርካት ህዝበ ክርስቲያንን ያስቆጣው  ለኦሮሚያ ክልል 17 ጳጳሳት እንዲሁም 9 ጳጳሳት ከኦሮሚያ ውጭ በጥቅሉ 26 ጳጳሳትን ከቤተ ክርስቲያን ሥርዓተ ቀኖና ውጭ መሾማቸው ነው፡፡

አቡነ ሳዊሮስ በዓለ ሲመቱ ከተከናወነ በኋላ በሰጡት መግለጫ ሲመቱን ለመፈጸም ያበቋቸውን አስገዳጅ ሁኔታዎች መዘርዘራቸው ይታወሳል። ከተዘረዘሩት ምክንያቶችም መካከል በበርካታ የሀገሪቱ ክፍሎች የቤተክርስቲያኗ ተከታዮች አገልግሎት ለማግኘት ያስችላቸው ዘንድ አከባቢያቸውን የሚያውቁ እንዲሁም ቋቋቸውን የሚናገሩ አገልጋዮች ሊኖራት እንደሚገባ አመላክተው ይህ ባለመደረጉ ቤተክርትሲያኗ በተለይም በኦሮምያ እና ደቡብ ክልል በሚሊዮን የሚቆጠሩ አማኞቿን አጥታለች የሚለው ይገኝበታል።

የጳጳሳቱ ሹመቱ ከሲኖዶሱ እውቅና ውጭ የተደረገ ህገ-ወጥ ሹመት ነው ያሉት የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትሪያርክ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ድርጊቱ “በቤተ ክርስቲያን ላይ ያነጣጠረ ታላቅ ክስተት” ነው በማለት አስቸኳይ ምልአተ ጉባኤ መጥራታቸው ይታወሳል፡፡አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.