አዲስ አበባ፣ ጥር 24/ 2015 ዓ.ም፡- ከደቡብ ክልል ቡርጂ በመነሳት አማሮ ልዩ ወረዳዎችን በማቋረጥ ወደ ዲላ ከተማ በመጓዝ ላይ በነበሩ አምስት ሰዎች ላይ ታጣቂዎች በከፈቱት ተኩስ ሁለት ሰው ሲገደል አራት ሰው መቁሰሉን ቪኦኤ ዘግቧል፡፡
ዜና አውታሩ ያናገራቸው ነዋሪዎች እና የአካባቢው ባለሥልጣናት በገላና ወረዳና በአማሮ ወረዳ አዋሳኝ አከባቢም የአማሮ ልዩ ወረዳ ነዋሪ እና የ11ኛ ክፍል መገደሉን ገልፀዋል።
የአማሮ ልዩ ወረዳ ፖሊስ አዛዥ፣ ጥቃት የደረሰባቸው ሰዎች ከቡርጂ ተነስተው ወደ ዲላ በመጓዝ ላይ እያሉ ተኩስ እንደተከፈተባቸው ገልፀዋል፡፡ አክለውም አሁን ላይም ወደ ዶረባድ አካባቢ ተኩስ እንዳለ ገልፀዋል፡፡
የቡረጂ ልዩ ወረዳ ፖሊስ አዛዥ ምክትል ኮማንደር ደስታ ባንጌ እና የአማሮ ልዩ ወረዳ ፖሊስ አዛዥ ጥቃቱን ያደረሱት ታጣቂዎች ምንነታቸው በግልፅ ባይታወቅም የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት (መንግስት ሸኔ ብሎ ያሚጠራቸው) አባላት መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ምክትል ኮማንደር ደስታ በጥቃቱ በሁለት ወንድና አንድ ሴት ላይ ከባድ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው መሆኑንና አንድ ወንድ ላይ ቀላል የአካል ጉዳት ደርሷል በማለት ገልፀው በንብረት ላይም ውድመት ደርሷል ብለዋል፡፡
ታጣቂዎቹ ዘመናዊ መሳሪያ የታጠቁ ናቸው የሚሉት አንድ የስፍራው ነዋሪ አርሶ አደሩ ሊቋቋማቸው እንዳልቻለ በመግለፅ የመንግስት የፀጥታ አካላት ጥቃት ከተፈፀመ በኋላ ነው በስፍራው የሚደረሱት ሲሉ ቅሬታቸውን ገልፀዋል፡፡