ዜና፡ ቅዱስ ሲኖዶስ መንግስት የቤተ ክርስቲያኒቱን መብት የማያስከብር ከሆነ ከቅዱስ ፓትርያርኩ ጀምሮ ምእመናን የሚሳተፉበት ሰላማዊ ሰልፍ እንደሚካሄድ አስታወቀ፤ ጠ/ ሚኒስትር አብይ አህመድ በሰጡት ማብራሪያ ላይ እርምት እንዲሰጡ አሳሰበ

                                                                                                                                                 

አዲስ አበባ፣ጥር 25/ 2015 .ም፡የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ መንግሥት በሕገ መንግሥቱ የተጣለበትን ኃላፊነት በመወጣት የቤተ ክርስቲያኒቱን ተቋማዊ ልዕልና እንዲያስጠብቅ እንዲሁም ህገ ወጡን ድርጊት ተገቢውን እርምት እንዲሰጥ አሳስቦ ይህ የማይሆን ከሆነ ግን ከቅዱስ ፓትርያርኩ ጀምሮ ብፁዓን አበው ሊቃነጳጳሳት፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ አገልጋይ ካህናትና ምእመናን ጭምር የሚሳተፉበት ሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ሰላማዊ ሰልፍ እንደሚካሄድ አስታወቀ፡፡

በቤተክርስቲያኗ ወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ በጥር 23 ቀን 2015 ዓ.ም ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ለሚኒስትሮችና ለካቢኔዎቻቸው በሰጡት የወቅታዊ ጉዳይ ማብራሪያ አስመልክቶ ቅዱስ ሲኖዶስ ትላንት ማታ የምላሽ መግለጫ ሰጥቷል። በመግለጫውም ቤተክርስቲያኗ አቋሟን በዝርዝር ያስቀመጠች ሲሆን ጠ/ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው የጠቀሷቸው ማብራሪያዎች አሳሳቾች ናቸው ስትል ተችታለች። እርምት እንዲወሰድባቸውም አሳስባለች።

ጠ/ሚኒስትሩ ባጋሩት የ 36 ደቂቃ ርዝማኔ ባለው  የቪዲዮ ማብራሪያ በርካታ ነጥቦችን ያነሱ ሲሆን፣  ”በአሁኑ ወቅት በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የተፈጠረው ጉዳይ በጣም ቀላል ነው፣ በንግግር የሚፈታ ነው” በማለት ተናግረዋል፡፡ በዚህ ንግግራቸው ላይ የቅዱስ ሲኖዶሱ መግለጫ ጠ/ሚኒስትሩ ዱዳዩን ያዩበት መንገድ ፍጹም ተቀባይነት የለውም፣ ይህ አገላለጽ በቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ ውስጥ ጣልቃ እንደመግባት እና ቤተ ክርስቲያን የምታስተላልፋቸውን ሀይማኖታዊና ቀኖናዊ ውሳኔዎች ያላቸውን ውጤት ወደ ጎን የተወ መሆኑን ቤተ ክርስቲያን ታምናለች ሲል ምላሽ ሰጥቷል፡፡  

ከዚህም አልፎ ሁለቱም ወገን ውስጥ እውነት አለ፣ ሁለቱም አባቶቻችን ናቸው፣ ለማንም አንወግንም፤ ማንም የካቢኔ አባል እዚህ ውስጥ እጁን እንዳያስገባ፣ የሚሉት አገላለጾች መንግስት ሕገ-መንግሥታዊ ጥስት በመፈጸም በሃይማኖታዊ ጉዳይ ጣልቃ መግባቱንና በእርሱም ይሁንታ መፈንቀለ ሲኖዶስ እየተከናወነ እንዳለ እምነት የሚያሳድር በመሆኑ ይህ አድራጎት እንዲታረምና ኃላፊነቱ እንዲወስድ መግለጫው አሳስቧል።

ጠ/ሚኒስትሩ ቀደምት ሥርዓተ መንግሥታትን በዋቢነት በመጥቀስ አሁናዊው የብልጽግና መንግሥት በውጭ የነበረውን የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ቅዱስ ሲኖዶስ በእርቅ አንድ ማድረጋቸውን ሲገልጹ በሀገር ውስጥ ሁለት መንበርና ሁለት የፕትርክና መሪነት እንደነበረ የሰጡትን ማብራሪያ ተቀባይነት የለውም ብሏል። በድርድር ሃይማኖታዊ መመሪያችሁን ጥሳችሁ ቀኖናዊ ሥርዓታችሁን አፍርሳችሁ፤ አስተዳደራዊ መዋቅራችሁን ንዳችሁ ተቀብሏቸው እንደማለት የሚያስቆጥር ማብራሪያ አዘል መመሪያ እርምት እንዲሰጥበት ቅዱስ ሲኖዶስ አክሎ አሳስቧል፡፡

በተጨማሪም በቋንቋ የመገልገል መብትን መንግሥት ማፈን አይችልም በማለት ጠ/ ሚኒስትሩ የሰጡት ማብራሪያን በተመለከተ፣ ቤተክርስቲያኗ የቋንቋ አገልግሎትን እንደተቃወመችና ለአገልግሎቱም በሯን እንደዘጋች በሚያስቆጥርና ከእውነታው የራቀና የሕገወጥ ሥልጣን ፈላጊዎችን ሕገወጥ አካሄድና መግለጫ እውቅና የሚሰጥ አድራጎት በመሆኑ እርምት እንዲሰጥበት ቅዱስ ሲኖዶስ በጽኑ ያሳስባል ሲል መግለጫው አስቀምጧል።

ጠ/ሚኒስትሩ በክልል ትግራይ የተከሰተውን ጦርነት ተከትሎ በክልሉ ለሚኖሩ የቤተ ክርስቲያኒቱ አባቶች በወቅቱ ሰጥተውን የነበረውን መግለጫ አንድም ተቃውሞ ሳይቀርብበት አሁን በኦሮምያ ለተከሰተው ተቃውሞ አግባብ አይደለም በማለት የሰጡትን ማብራሪያ በተመለከተ፣ የትግራይ አአባቶጭ የቤተ ክርስቲያኒቷን ሕጎችና ቀኖናዎች ጥሰው ሕገወጥ ሲኖዶስ አልመሠረቱም፤ ጳጳሳትንም አልሾሙም፣ እውነታው ይህ ሆኖ እያለ አሁን የተፈጸመውን ሕገወጥ ሹመትና መፈንቅለ ሲኖዶስ ሕጋዊ ሽፋን እንዲኖረው ለማድረግ በሚያስመስል ሁኔታ ሁለቱ የማይገናኙ ድርጊቶችን በንጽጽር የተሰጠው ማብራሪያ እርምት እንዲሰጥበት ሲል ሲኖዶስ በመግለጫው በጥብቅ አሳስቧል ፡፡

የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን በተመለከተ የሲኖዶሱ መግለጫ፣ መንግሥት ቋሚ የገቢ ምንጭ የሚያገኝበት የቱሪስት መዳረሻ መሆኑ እየታወቀ የቤተ ክርስቲያን ሀብት ብቻ ተደርጎ ከፈረንሣይ መንግሥት የተገኘውን ድጋፍ ለቤተ ክርስቲያን እንደተሰጠ ልዩ ጥቅም በማድረግ ማቅረብ አግባብነት የለውም ብሏል፡፡

ጠ/ሚኒስትሩ በቅዱስ ሲኖዶሱ እና ውጭ ባሉ አባቶች መካከል ሲካሄድ የነበረውን የዕርቅ ሒደት እልባት እንዲያገኝ ማድረጋቸው፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ይዞታዎችና ሕንጻዎች መካከል 4ኪሎ የሚገኙትን ሁለቱን ቀደምት ሕንጻዎች ለቤተ ክርስቲያን መመለሳቸው፣ በተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ሀገረ ስብከት ለሚገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሕንጻ መሥሪያ ቦታ ማድረጋቸው፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሀገር መሆኗን መግለጻቸው፣ የቤተ ክርስቲያኗ መዳከም ጉዳቱ ለቤተ ክርስቲያኗ ብቻ ሳይሆን ለሀገረ መንግሥቱም ጭምር መሆኑን መግለጻቸው፣ አግባብነት ያለውና ለዚህም  አድራጎታቸው ቤተ ክርስቲያናችን በወቅቱ በእውቅና ሽልማት አጅባ አመሰግናለች ብሏል መግለጫው።

በመጨረሸም መግለጫው “ ችግሩ ተፈቶ የቤተ ክርስቲያኒቱ መብት እስኪረጋገጥ ድረስ ያለማቋረጥ እስከ ሕይወት መስዋዕት ድረስ በመክፈል ለአለም ህዝብ የምናሳውቅ ይሆናል” ሲል  አስጠንቅቋል፡፡አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.