ዜና፡ ከመተማ -ገላባት ያለው የኢትዮ-ሱዳን ደረቅ ወደብ በዛሬው ዕለት ተከፍቶ አገልግሎት መስጠት ጀምረ


በብሩክ አለሙ @Birukalemu21

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 15፣ 2014 ዓ.ም ፡-የምእራብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ቢክስ ወርቄ የደረቅ ወደቡ ለአገልግሎት ክፍት መሆኑን በተመለከተ ባደረጉት  ንግግር “በኢትዮጵያ እና ሱዳን መካከል ዘመናትን ያስቆጠረው ወንድማማችነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሁሉም ኢትዮጵያዊና የአካባቢው ማህበረሰብ የድርሻችንን ልንወጣ ይገባል” ብለዋል።

ዋና አስተዳዳሪው አክለውም በሱዳን እና ኢትዮጵያ መካከል ዘመናትን ያስቆጠረው ወንድማማችነት ነገም የሚቀጥል የማይበጠስና የጸና እንዲሆን ሁሉም ኢትዮጵያዊና የአካባቢው ማኅበረሰብ ተባብረን የድርሻችንን ልንወጣ ይገባል ብለዋል።

አቶ ቢክስ አያይዘውም ከድንበር መዘጋት ጋር ተያይዞ የነበረው ችግር የኢትዮጵያ መንግሥት ባስቀመጠው በሰላማዊ አማራጭ በውይይት የመፍታት አካሄድን ለማጠናከር፤ አሁንም ከሕዝባችን ጋር የአካባቢያችንን ሰላም ነቅተን እንጠብቃለን ማለታቸውን አሚኮ ዘግቧል።

በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው፤ በእኛ በኩል የዉስጥ ችግራችንን ማጤን እና በዉስጣችን ተሰግስገዉ ሰላማችንን በማደፍረስ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት በሴራ ለማበላሸት ለሚሠሩ ኃይሎች መጠቀሚያ ከመኾን መቆጠብ ይገባል ያሉት ዋና አስተዳዳሪው  ከዚህ አንጻርም ተደራጅተዉ ለመዝረፍ ሙከራ የሚያደርጉም ሆነ የጠላት ዓላማ ማስፈጸሚያ ለመኾን የሚሠሩ ኃይሎችን መልክ ለማስያዝ የጀመርነውን ሥራ አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።

ኢትዮጵያና ሱዳን በድንበር የተነሳ በተደጋጋሚ ግጭት ሲፈጠር መቆየቱ ይታወቃል፡፡ ኢትዮጵያ በደርግ ወታደራዊ መንግስት መመራት ከጀመረችበት ጊዜ ጀምሮ ሁለቱ አገሮች በ1997 ዓ.ም በአልፋሸግና በአካባቢው ላይ ሁለንተናዊ ተቀባይነት ያለው አደረጃጀት እስከደረሱበት ጊዜ ድረስ  ለተከታታይ 33 ዓመታት ጠበኛ ሆነው ቆይተዋል። 

ታህሳስ 19 ቀን 2013 ዓ.ም. በወቅቱ የምዕራብ ጎንደር አስተዳደር የነበሩት እና በአሁኑ ሰዓት ግን የአማራ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ሀላፊ የሆኑት አቶ ደሳለኝ ጣሰው የሱዳን ሀይሎች ሰፊ መሬት በመያዝ ነዋሪዎችን እየዘረፉ እና እየገደሉ ነው ሲሉ ወቅሰዋል። ሃላፊው አክለውም ከ25.5 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ የሚገመት ንብረት መዘረፉን፣ ከ400 እስከ 500 አባወራዎች መፈናቀላቸውን እንዲሁም  ከሰላም በር ቀበሌ 1,750 ሰዎች መፈናቀላቸውንና መንደራቸው በእሳት መውደሙን ገልጸዋል።

ሁለቱ ሀገራት በቅርቡ በአካባቢው በተከሰቱ ግጭቶች ላይ የተለያዩ አመለካከቶች ያላቸው ቢሆንም፣ በዚህ ዓመት የመጀመሪያዎቹ ሁለት ወራት ሁለቱም ሀገሮች በድንበር አካባቢ ወታደራዊ ኃይል ማሰማራታቸውን አዲስ ስታንዳርድ ተገንዝባለች። ግጭቶቹ በተከሰቱባቸው  በኢትዮጽያ እና ሱዳን ድንበር አከባቢ አሁንም ወታደራዊ ፍጥጫ እንዳለ ከመከላከያ ሰራዊት ታማኝ የመረጃ ምንጭ አረጋግጦልናል። አካባቢው እስካሁን ድረስ በሱዳን ጦር ስር እንደሚገኝም ምንጫችን ተናግሯል።

ምንም እንኳን  ስምምነቱ በይፋ ባይፀድቅም፣ በ2000 ዓ.ም. ኢትዮጵያ እና ሱዳን፤ በፕሬዚዳንት ኦማር አልበሽር እና በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አማካኝነት የመጨረሻው የድንበር ስምምነት እስከሚጠናቀቅ ድረስ የሁለቱም ሀገራት ዜጎች በጋራ መሬቱን ማረስ የሚችሉበት በአንፃራዊ ምቹ የሆነ የመሬት አጠቃቀም ስምምነት ላይ ደርሰው ነበር።  በሁለቱም ሀገራት የተፈጠረው የፖለቲካ አለመረጋጋት የአመራር ለውጦችን ያስከተለ ሲሆን የአል-ፋሻጋ ጉዳይም ወደ ቀድሞው ተደጋጋሚ ግጭቶች እንዲመለስ አድርጎታል። ግልጽ የሆነ የድንበር ወሰን ባለመኖሩ እና የድንበሩ ተለዋዋጭ ባህሪይ የተነሳ በሁለቱ ሀገራት ለረጅም ጊዜ በዘለቀው አለመግባባትና ግጭት በአካበቢው የሚኖሩ አርሶ አደሮች ሰለባ ሆነዋል። አስ


No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.