ዜና፡ ኦፌኮ ኢትዮጵያ “በፖለቲካ ውድቀት፣ የእርስ በርስ ጦርነት እና የኢኮኖሚ ቀውስ” እየተናጋች ስለሆነ እውነተኛ ብሔራዊ ውይይት እንዲደረግ ጠየቀ

በብሩክ አለሙ @Birukalemu21

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 5/2014:- የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ኢትዮጵያ በፖለቲካ ውድቀት፣ የእርስ በርስ ጦርነት እና የኢኮኖሚ ቀውስ እየተናጋች መሆኗን ገልፆ ጦርነቱ እንዲቆም እና ግጭቱን የሚያስቆም እና ሀገሪቱን ወደ ፖለቲካዊ ለውጥ የሚያመጣ እውነተኛ ብሔራዊ ውይይት  እንዲደረግ ጠይቀ።  

የፓርቲው አመራሮች ትናንት ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ከአንድ ዓመት ተኩል በላይ ባስቆጠረው የእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት በሕዝብ ላይ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን ገልፀው ለመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሞት፣ ለሚሊዮኖች መፈናቀል እና በመቶ ቢሊዮን ብር ለሚገመት ንብረት ውድመት ምክንያት ሆኗል ብለዋል። አመራሮቹ አክለውም “ይህም አገሪቱን ወደ ፍፁም ውድቀት እንድታመራ አድርጓታል። የትግራይ፣ የአማራ፣ የአፋር፣ የኦሮሚያ እና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች በዋነኛነት በጦርነቱ የተጠቁ  ሲሆኑ ሁሉም የአገሪቱ ክልሎች በጦርነቱ መዘዘት እየተሰቃዩ ይገኛሉ” ሲሉ ገልጸዋል።

“በደቡብ ኦሮሚያ በቦረና ዞን ዙሪያ የኦሮሞ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ከብቶቻቸውን በድርቅ አጥተው ልጆቻቸውን እንደ በሬ በመጥመድ መሬታቸውን ለማረስ ተገደዋል። የኦሮሞ ህዝብ በረዥም ታሪኩ እንዲህ አይነት ሰቆቃ አይቶ አያውቅም” ሲል ኦፌኮ ትናንት በመግለጫው የችግሩን አሳሳቢነት አብራርቷል። 

የትግራይ፣ የአማራ፣ የአፋር፣ የኦሮሚያ እና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች በዋነኛነት በጦርነቱ የተጠቁ  ሲሆኑ ሁሉም የአገሪቱ ክልሎች በጦርነቱ መዘዘት እየተሰቃዩ ይገኛሉ”

ኦፌኮ

እንደ ኦፌኮ ገለፃ በኦሮሚያ እየተካሄደ ባለው የእርስ በርስ ጦርነት ከ297 በላይ ንፁሀን ዜጎች በመንግስት ታጣቂዎች ተገድለዋል፡፡ ይህም “ከአለም አይን ተደብቋል ” ያለው ፓርቲው ጦርነቱ ከ500,000 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች መፈናቀል፣ ለቤቶች ማቃጠል፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ትምህርት ቤቶች መዘጋት እና ሆስፒታሎች እና የጤና ጣቢያዎች አገልግሎት እንዳይሰጡ ምክንያት ሆኗል ብሏል።

“ኢትዮጵያ ዛሬ የገጠሟት ቀውሶች “ቀጥታ የማይነጣጠሉ ጉዳዮች ናቸው” ሲል  የገለፀው ኦፌኮ ፣ “መፍትሄውም ጦርነቱን በማስቆም ችግሮቻችንን ወደ ፖለቲካ ድርድር ማምጣት  ነው” ብሏል። አክሎም “በአሁኑ ወቅት በብሔራዊ ውይይት ስም እየተካሄደ ያለው እንቅስቃሴ በሀገራዊ ውይይቱ ላይ  መሳለቂያ እና ነባራዊ ችግሮችን የበለጠ ሊያወሳስብ የሚችል አደገኛ እርምጃ ነው፡፡ ኮሚሽኑም ሆነ ሒደቱ ነፃ ወይም አካታች አይደሉም ” ብሏል።

ፓርቲው የእርስ በርስ ጦርነት እየተካሄደ አገር አቀፍ ውይይት ሊካሄድ እንደማይችል ገልጾ፣ መንግሥት ጦርነቱን በማቆም  ጉዳዩን ወደ ፖለቲካዊ ድርድር እንዲያቀርብና የሕዝቡን ስቃይ እንዲያቀል  ጠይቋል።አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.