አዲስ አበባ :ሰኔ 2 /2014 ዓ.ም. ፡- ኤስ ኦ ኤስ የህጻናት መንደር በጦርነቱ ምክንያት ከፍተኛ ሰብዓዊ ጉዳት ለደረሰባቸው ከ260ሺህ በላይ ዜጎች የሚውል የ145 ሚሊየን ብር የድጋፍ ፕሮጀክት በይፋ ማስጀመሩን አዲስ ማለዳ የዜና አውታር ዘገበ።
በኢትዮጵያ የኤስ ኦ ኤስ የህጻናት መንደር ዋና ዳረሬክተር አቶ ሳህለማርያም አበበ እንደተናገሩት ድጋፉ በአማራ፣ አፋርና ትግራይ ክልሎች የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ የሚያደርግ ሲሆን ፕሮግራሙ በሁለት አመት ጊዜ ውስጥ የሚተገበር ይሆናል፡፡
እንደዘገባው ፕሮጀክቱ በሶስት ክልሎች ተግባራዊ ከሚደረገው 4 ሚሊዮን ዶላር ውስጥ በአማራ ክልል በሚደረግ የ145 ሚሊየን ብር ድጋፍ የተጀመረ ሲሆን፤ በቀጣይ ደግሞ በትግራይ እና አፋር ክልሎች ለሚገኙ እና በጦርነቱ ምክንያት ከፍተኛ ሰብዓዊ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች ቀሪው 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ዩሮ ድጋፍ ተደራሽ እንደሚሆን ዳይሬክተሩ አክለው ገልፀዋል።
በፕሮጀክቱ መሰረት ሰሜን ሸዋ፣ ሰሜን ወሎ፣ አድዋ፣ መቀሌ እና ምስራቅ ሀረርጌ ዞኖች ተጣቃሚ እንደሚሆኑ የተገለፀ ሲሆን የዚህ ፕሮጀክት ዋነኛ አላማ ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ዜጎች ሰብአዊ ድጋፍ የሚያገኙበትን መንገድ ማመቻቸት፣ በጦርነቱ ምክንያት ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸውን የትምህርት ተቋማት መልሶ መገንባት እንዲሁም በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸው ሴቶች እና ህጻናት ሰብአዊ ድጋፍ የሚውልና ለገበሬዎች ዘር ከማቅርብ እስከ ለእርሻ የሚውሉ በሬዎች ድረስ ድጋፍ ለማቅረብ ነው፡፡ መተጨማሪም የምግብ አቅርቦት ችግር ላለባቸው እንደ ሰቆጣ ባሉ ሶስት ወረዳዎች የምግብ አቅርቦት ይፈጸማል ነው የተባለው፡፡
በፕሮግራሙ ላይ የተገኙት የሲቨል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክትል ዳሬክትር አቶ ፋሲካው ሞላ እንደተናገሩት ባለፉት ሶስት አመታት ከ 2 ሺህ በላይ አዳዲስ የሲቭል ማህበረሰብ ድርጅቶች መመዝገባቸውን ተናግረው ድርጅቶቱም ከፍተኛ ስራ እየሰሩ ይገኛሉ ብለዋል፡፡ በዚህም መሰረት በሀገሪቱ በተከሰተው ጦርነት ዜጎች ሰብአዊ ድጋፍ እንዲያገኙ ባደረጉት ጥረት ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡ ድርጅቶቹ በአፋር እና በትግራይ ክልል ከ 440 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አድርገዋል ሲሉም ገልጸዋል፡፡
ኤስ ኦ ኤስ ኢትዮጵያ የህጻናት መንደር አሁን ላይ በሰባት ከተሞች 24 ያህል ፕሮጀክቶችን ቀርጾ ተግባራዊ እያደረገ እንደሚገኝ ዘሬ ባስጀመረው በመድክ ላይ ተገልጿል፡፡ በፕሮጀክቱ በአማራ ክልል ለሚገኙ ከ231 ሺህ በላይ የሚሆኑ ሰዎችን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተጠቃሚ የሚያደርግ ሲሆን፤ በክልሉ በተመረጡት አካባቢዎች ላይ የሚሰሩት ሥራዎች ከተጠናቀቁ በኃላ በሚገኙ ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፎች በአፋር እና ትግራይ ክልሎች ላይ ድጋፍ የማድረሱ ሥራ እንደሚቀጥልም ይፋ ተደርጓል።አስ