ዜና፡ ኢትዮጵያ በትግራይ ጦርነት የተፈጸሙ ወንጀሎች ላይ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሚደረገው ምርመራ እንዲቋረጥ ድጋፍ እያሰባሰበች መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 21/ 2015 ዓ.ም፡– የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ጦርነት ወቅት የተፈጸሙ ሰብአዊ ወንጀሎችን ለማጣራት የሚካሄደው ምርመራ እንዲቆም የሚጠይቅ ረቂቅ የውሳኔ ሀሳብ ለተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት አባላት ማሰራጨቱን ሮይተርስ የዜና ወኪል ምንጮቹን ዋቢ በማድረግ አስታወቀ። እርምጃውም የምርመራው ውጤት ይፋ እንዳይወጣ እና በምክር ቤቱም ለክርክር እንዳይቀርብ ሊያግድ የሚችል መሆኑንም አመላክቷል።

መረጃውን ከአምስት ዲፕሎማት ምንጮቼ አገኘሁት ያለው የዜና አውታሩ ጉዳዩ በምእራባውያን እና በአፍሪካ ሀገራት መካከል ልዩነት ሊፈጥር ይችላል የሚል ስጋት መፍጠሩን ጠቁሟል። አለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ኤክስፐርቶች ኮሚሽን ስራውን አለማጠናቀቁን ሮይተርስ በዘገባው አስታውቋል። በትግራይ በተካሄደው ጦርነት በሺዎች የሚቆጠሩ መሞታቸውን እና በሚሊዮኖች ከቀያቸው መፈናቀላቸውን ያመላከተው ዘገባው ተፋላሚ ሀይሎቹ በተፈጸሙት የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ዙሪያ አንዱ አንዱን ተጠያቂ በማድረግ መወነጃጀላቸውን አስታውቋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ትናንት የካቲት 20 ቀን 2015 52ኛ ጠቅላላ ጉባኤውን የጀመረ ሲሆን በኢትዮጵያው የትግራይ ጦርነት ወቅት የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እና የጦር ወንጀሎች ዙሪያ እንደሚወያይ ምክር ቤቱ በድረገጹ ይፋ ባደረገው መርሃ ግብር አስታውቋ። በመርሃ ግብሩ መሰረት የኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ምክር ቤቱ የሚወያየው በአራተኛው ሳምንት መጋቢት 11 ቀን 2015 መሆኑም ተገልጿል።

የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ያቋቋመውን የባለሞያዎች ኮሚሽን የኢትዮጵያ መንግስት ከመጀመሪያው ጀምሮ ለፖለቲካዊ አላማ የተቋቋመ ነው በሚል ሲቃወመው እንደነበር ተመላክቷል። በኢትዮጵያ የተዘጋጀው ረቂቅ የውሳኔ ሀሳብ በይፋ ለምክር ቤቱ አባል ሀገራት አለመቅረቡን ዘገባው አስታውቋል። ኢትዮጵያ ሀሳቧን እንድትቀይር ለማሳመን ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ የዜና አውታሩ ጉዳዩን በቅርበት ከሚያውቁ ሁለት ዲፕሎማቶች መስማቱን አካቷል።

በቅርቡ የኢትዮጵያ መንግስት ለአጣሪነት የተመደበው ኮሚሽን በጀት እንዳይመደብለት ያቀረበውን ሃሳብ በአብላጫ ድምጽ ውድቅ ቢደረግም አብዘሃኛዎቹ የአፍሪካ ሀገራት ተወካዮች ግን ለኢትዮጵያ መንግስት ድጋፍ መስጠታቸውን ዘገባው አውስቷል። ይህም ጉዳዩ ቀርቦ ምክር ቤቱ ወደ ድምጽ መስጠት የሚያመራ ከሆነ በአባላቱ ሀገራት መካከል ከፍተኛ መከፋፈል ውስጥ እንደሚያስገባቸው እና ከመጀመሪያው ጀምሮ ለኮሚሽኑ መቋቋም ድጋፍ ሲሰጥ በነበረው የአውሮፓ ህብረት ከአፍሪካ ጋር ያለው ግንኙነት ሊያሻክረው እንደሚችል ስጋት መፈጠሩን ዘገባው አስታውቋል።

ትንቅነቅ እንደሚፈጠር አንድ ዲፕሎማት ገልጸውልኛል ያለው ዘገባው በምክር ቤቱ የአሜሪካ ተወካይ የሆኑት ሚካኤል ቴይለር ኢትዮጵያ የኮሚሽኑ ተልእኮ እንዲቋረጥ እንደምትፈልግ አረጋግጠው ለወደፊቱ የሚኖረው አንድምታ አደገኛ መሆኑን በመግለጽ ኢትዮጵያ አሁን ለያዘችው የሰላም መንገድ እና እርምጃ የኮሚሽኑ ተልእኮ መቋረጡ ጠቀሜታ ይኖረዋል ብለው እንደማያምኑ መናገራቸውን አመላክቷል።አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.