አዲስ አበባ፣ ጥር 3/ 2015 ዓ.ም፡- አዲስ “ቤተ ክህነት” አቋቁመናል በማለት ያሳወቁ ጳጳሳት በአንዳንድ ቦታዎች በኃላፊዎች ድጋፍ ጭምር በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል ከተሞች የሚገኙ ሀገረ ስብከቶችን መያዛቸውን ተከትሎ ይህን ድርጊት በተቃወሙ ሰዎችና የሃይማኖት መሪዎች ላይ በመንግሥት የጸጥታ አባሎች በርካታ የሰበዓዊ መብት ጥሰት መፈፀሙን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታወቀ፡፡
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ዛሬ ባወጣው መግለጫ ተፈፅሟል ያላቸውን የመብት ጥሰቶች የዘረዘረ ሲሆን በመንግሥት የጸጥታ አባሎች ተመጣጣኝ ባልሆነ ኃይል አጠቃቀም በጥይት እና በድብደባ የተፈጸሙ ግድያዎች፣ ከሕግ ውጭ የተፈጸሙ እስሮችና የእንቅስቃሴ ገደቦች መተግበራቸውን ገልጧል፡፡
አክሎም ሲኖዶሱ ያቀረበውን የጥቁር መልበስ ጥሪ የተቀበሉ ሰዎች ላይ የተፈጸሙ እስሮች፣ ከአገልግሎት እና ከሥራ ቦታ ማግለልና ማንገላታት ፍጹም ተገቢ ያልሆኑ እና የዜጎችን በሕይወት የመኖር፣ በነጻነት ሃይማኖታቸውን እና ሐሳባቸውን የመግለጽ ሕገ መንግሥታዊ መብቶችን የሚፃረሩ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች መፈፀማቸውን አረጋግጫለው” ብሏል፡፡
አዲስ የተሾሙት ጳጳሳቱ የሻሸመኔ ደብረ ስብሐት ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያንን ለመያዝ ያደረጉትን እንቅስቃሴ ተከትሎ በመንግሥት ጸጥታ አባላት በተወሰደ ተመጣጣኝ ያልሆነ የኃይል እርምጃ እና ከጸጥታ አባሎቹ ጋር ሲተባበሩ በነበሩ ሰዎች ቢያንስ ስምንት ሰዎች በጥይትና በድብደባ መገደላቻውን ማረጋገጡን ይፋ አድርጓል፡፡
አክሎም ቁጥራቸው ገና በትክክል ያልታወቀ ሰዎች ለተለያየ ዓይነትና መጠን የአካል ጉዳት መዳረጋቸውን እንዲሁም በርካታ ሰዎች ለተለያየ ጊዜ መጠን መታሰራቸውን ማረጋገጡን በመግለጫው አስታውቋል፡፡
ስለሆነም መንግሥት የተሟላና ተገቢውን ማጣራት አድርጎ ተገቢውን ሕጋዊ እርምጃ ሊወስድ እና የተጎዱትንም ሊክስ ይገባል ሲል ኮሚሽኑ ገልጧል። በተጨማሪም የመንግሥት ጸጥታ ኃይሎች ሰላማዊ ተቃውሞ በሚያደርጉ ሰዎች ላይ ኃይል ከመጠቀም፣ ከማንገላታት፣ ከሕገ ወጥ እስር እና የሰዎችን እንቅስቃሴ ያለበቂ ምክንያት ከመገደብ መቆጠብ ይኖርባቸዋል ሲል አሳስቧል፡፡
እየተከሰተ ያለው ችግር አስቸኳይ እልባት ካላገኘ ለከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ሥጋት ነው ያለው ኢሰመኮ የተፈጠረው ችግር የሃይማኖት ነጻነት መሠረታዊ መብትና የሃይማኖት ጥበቃ ሕገ መንግሥታዊ መርህ መሠረት በቤተ ክርስቲያኗ የውስጥ ሥርዓት መሠረት እንዲፈታ ጥረት እያደረኩ ነው ብሏል፡፡
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ “የሀገርን ሰላም እና ደኅንነት መሠረት በማድረግ፣ የኃይማኖቶችና ሌሎችም ነጻ ተቋሞችን ነጻነት ማክበርና መጠበቅ አስፈላጊነት በማጤን፣ ሁሉም ሰው እና ማኅበረሰብ፣ ለችግሩ መፍትሄ ለመፈለግ የሚደረገውን ጥረት እንዲያግዙ” ጥሪ አቅርበዋል።አስ