ዜና፡ አሜሪካ የኢትዮጵያ፣ የኤርትራ እና የአማራ ሃይሎች በትግራዩ ጦርነት “በሰብዓዊነት ላይ ወንጀል” መፈፀማቸውን ገለፀች፤ ሁሉም ተፋላሚ ሀይሎች “የጦር ወንጀል” ፈፅመዋል ብላለች

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 12/ 2015 ዓ.ም፡– አሜሪካ የ2022 አመት በአለም ላይ የታዩ የሰብአዊ መብት ጉዳዮቹን በተመለከተ በትላንትናው ዕለት ይፋ በተደረገችበት ሪፖርት የኢትዮጵያ፣ የኤርትራ እና የአማራ ሃይሎች በትግራዩ ጦርነት “በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል” መፈፀማቸውን አስታወቀች፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በትግራይ ተጀምሮ ለሁለት አመት በዘለቀው እና ወደ አማራ እና አፋር በተስፋፋው ጦርነት የትግራይ ሀይሎችን ጨምሮ ሁሉም ሀይሎች “የጦር ወንጀል” ፈጽመዋል ስትል ገልፃለች።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አንቶኒ ብሊንከን ሪፖርቱን ይፋ ሲያደርጉ “ከነዚህ ወነጀሎች ውስጥ አብዛኛዎቹ ድንገት ወይም በጦርነት የተከሰቱ ብቻ  ሳይሆኑ ታስቦ እና ሆን ተብሎ የተፈፀሙ ናቸው” ብለዋል፡፡

መስራቤታቸው ህጎችን እና እውነታውን በጥንቃቄ ካስተዋለ በኋላ የኢትዮጵያ የመከላከያ ሃይሎች፣ የኤርትራ መከላከያ ሃይሎች፣ የህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ ሃይሎች እና የአማራ ሃይሎች በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል በነበረው ጦርነት የጦር ወንጀሎችን መፈጸሙን በተመለከተ ድምዳሜ ላይ ደርሰናል ሲሉ አስታውቀዋል።

በተጨማሪም የኢትዮጵያ የመከላከያ ሃይል አባላት፣ የኤርትራ መከላከያ ሃይል አባላት እና የአማራ ሃይሎች አባላት ግድያ፣ አስገድዶ መድፈር እና ጾታዊ ጥቃቶችን፣ ስቃይ መፈጸምን ያካተተ በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል ፈጽመዋል ብለዋል። ብሊንከን አክለውም በምዕራብ ትግራይ ላይ  የአማራ ሀይሎች የፈጸሙት በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል ማፈናቀልን፣ በጉልበት ወደ ሌላ ቦታ ማስፈርን እና ዘር ማጽዳትን ያካተተ መሆኑን አስታውቀዋል።

አዲስ ስታንዳርድ ብሊንከን በአዲስ አበባ ተገኝተው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ መንግስታቸው የደረሰበትን ሪፖርት ለምን ይፋ አላደረገም የሚል ጥያቄ አንስቶ ነበር። በወቅቱ ለአዲስ ስታንዳርድ ቀጥታዊ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ በጦርነቱ ወቅት በንጹሃን ላይ የተፈጸሙ ሰብአዊ መብት ጥሰቶች ሀገራችው በተደጋጋሚ በግልጽ ስትኮንን እንደነበር እና በሁሉም ጎራ ያሉ ጥቃቱን የፈጸሙ ተጠያቂ እንዲሆኑ ማቅረቧን አውስተው ይህንን ጉዳይ ከአንድ አመት በፊት እኔ እራሲ ገልጨው ነበር ሲሉ ምላሽ መስጠታቸውን በዘገባችን ማካተታችን ይታወሳል።

የብሊንከን ሙሉ ንግግር

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.