ዜና፡ በጎፋ ዞን ከ 155 ሺህ በላይ ቤተሰብ አስቸኳይ የምግብ እርዳታ ይሻሉ ተባለ

በዞኑ የደረቀ ምርት፤ ፎቶ- የጎፋ ዞን ኮሙኑኬሽን

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 28/2015 .ም፡በጎፋ ዞን በሶስት ወረዳዎች ለተከታታይ አራት ዓመታት በአየር መዛባት ምክንያት በተከሰተው የምርት መቀነስ የተነሳ ከ 155 ሺህ  248 በላይ ቤተሰብ ለአስቸኳይ የምግብ እርዳታ መጋለጣቸውን የዞኑ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

የዞኑ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ውብዓለም ዝናቸው በዞኑ በዛላ፣ ዑባ ደብረፀሐይ ወረዳ እና በከፊል ደምባ ጎፋ ወረዳዎች በአየር መዛባትና ምርት መቀነስ ምክንያት አስቸኳይ የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልግ ገልፀው በዞን ማዕከል በተከፈተው የእርዳታ ማሰባሰቢያ የባንክ አካውንት የተሰበሰበ 1.4 ሚሊዮን ብር ወጪ ሆኖ በአስቸኳይ የእርዳታ እህል ግዥ በመፈፀም ለተጎጂዎች ተጨማሪ እርዳታ እንዲቀርብ ውሳኔ ማስተላለፉን ገልጸዋል።

በዞኑ ከሚገኙ ሌሎች ወረዳዎችም ኦይዳ ወረዳ የእህል እርዳታ እየተሰበሰበና እየቀረበ ሲሆን ከፌደራል አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽንም 3515 ኩንታል እህል እርዳታ ለዛላ ወረዳ ቢቀርብም በቂ አለመሆኑ ተገልጿል።

የዛላ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ከተማ ከበደ የአካባቢው አርሶአደሮች ከአካባቢው አልፎ ለማዕከላዊ ገበያ የሚያቀርቡና በትርፍ አምራችነታቸው የሚታወቁ ቢሆኑም ባለፉት ከሦስት ተከታታይ ዓመታትና ከዚያ በላይ በአየር መዛባት ምክንያት የአካባቢው ማህበረሰብ ለከፍተኛ ድርቅ መጋለጡን ተናግረዋል።

አክለውም በአሁኑ ሰዓት በወረዳው በነፍስ ወከፍ 67 ሺህ 907 የቤተሰብ አባላት ለአስቸኳይ የምግብ እርዳታ መጋለጣቸውን ዋና አስተዳዳሪው አስታውቀዋል። ዋና አስተዳዳሪው አስካሁን የተደረገው ድጋፍ ከተጎጂዎች ቁጥር አንፃር በጣም ዝቅተኛ በመሆኑ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የድጋፍ እጁን እንዲዘረጋም ጥሪ አቅርበዋል።

የአካባቢው አርሶአደሮች በበኩላቸው በተከሰተው ድርቅ ምክንያት ለከፍተኛ ችግር መጋለጣቸውን ገልጸው፣ የተከሰተው ችግር ከወረዳውና ከዞኑ መንግሥት አቅም በላይ በመሆኑ የፌዴራልና የክልሉ መንግሥት ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል።አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.