በብሩክ አለሙ @Birukalemu21
አዲስ አበባ፣ መስከረም 19/2015ዓ.ም፡- በጋምቤላ ከተማ ሰኔ 7 ቀን 2014 ዓ.ም. በክልሉ የጸጥታ ኃይሎች፣ በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (በተለምዶ ኦነግ ሸኔ) እና በጋምቤላ ነጻነት ግንባር (ጋነግ) መካከል የተደረገው ውጊያን ተከትሎ ከሰኔ 7 እስከ 9 ቀን 2014 ዓ.ም. በክልሉ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እንዲሁም ታጣቂ ኃይሎች ቢያንስ 50 ሲቪል ሰዎች በተናጠል እና በጅምላ መገደላቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታወቀ፡፡
ግድያዎቹን፣ የአካል ጉዳቶችን፣ የንብረት ጉዳት እና የዘረፋዎችን ድርጊት ሲመሩ እና ሲያስፈጽሙ የነበሩ ኃላፊዎች ላይ የሕግ ተጠያቂነት ሊረጋገጥ ይገባል ሲል የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ሲል አሳሰበ፡፡
ኮሚሽኑ በትላንትናው እለት መስከረም 18 ቀን 2015 ዓ.ም. ባወጣው ሪፖርት በድርጊቱ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ታጣቂ ቡድን፣ የጋምቤላ ነጻነት ግንባር ታጣቂ ቡድን፣ የጋምቤላ ክልል ልዩ ኃይሎች፣ ፖሊሶች፣ ሚሊሻዎች እና ተባባሪ ወጣቶች መሳተፋቸውን እና ድርጊቱን ሲመሩ እና ሲያስፈጽሙ የነበሩ ኃላፊዎችም እንደነበሩ ከሰኔ 20 እስከ ነሐሴ 16 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ ባደረገው የምርመራ ውጤት ማረጋገጡን ገልጿል፡፡
ሰኔ 7 ቀን 2014 ዓ.ም. ከቀኑ 7፡00 ሰዓት በኋላ እንዲሁም ሰኔ 8 እና 9 ቀን 2014 ዓ.ም. በዋናነት በክልሉ የጸጥታ ኃይሎች በተወሰዱ እርምጃዎች “የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች እና መሣሪያ በቤታችሁ እንዳለ ተጠቁመናል፤ የደበቃችሁትን መሣሪያ አውጡ” በሚል ምክንያት ሴቶችና የአእምሮ ሕመምተኞችን ጨምሮ ቢያንስ 50 ሲቪል ሰዎች በተናጠል እና በጅምላ ከፍርድ ውጪ መገደላቸውን፣ ቢያንስ 25 በሚሆኑ ሰዎች ላይ ቀላል እና ከባድ የአካል ጉዳት መድረሱን እንዲሁም በበርካታ ሰዎች ላይ የመደብደብና የማሰቃየት ተግባር መፈጸሙን መግለጫው ያስረዳል። በተጨማሪም በኦሮሞ ነፃነት
ንባር (ሸኔ)፣ በጋነግ፣ በክልሉ ልዩ ኃይሎች፣ ሚሊሻዎች እና ተባባሪ ወጣቶች በበርካታ ሰዎች ላይ የንብረት ውድመት እና ዘረፋ ተፈጽሟል ብሏል።
ውጊያው በተካሄደበት በሰኔ 7 ቀን 2014 ዓ.ም የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ሸኔ) እና ጋነግ ታጣቂዎችም በተኩስ ልውውጡ ወቅት “ተኩሳችሁብናል” በሚል ምክንያት እና በመንገድ ላይ ሲንቀሳቀሱ ያገኟቸውን ቢያንስ ሰባት ሲቪል ሰዎችን ገድለዋል፤ እንዲሁም በሲቪል ሰዎች ላይ ቀላል እና ከባድ የአካል ጉዳት አድርሰዋል፣ በበርካታ ሲቪል ሰዎችም ላይ የንብረት ዘረፋ እና ውድመት አድርሰዋል ያለው ኮሚሽኑ በተኩስ ልውውጥ ወቅት በየትኛው አካል እንደተገደሉ ያልታወቀ ስድስት ሰዎች ሞተዋል ብሏል።
ኮሚሽኑ በክልሉ የጸጥታ ኃይሎች የተገደሉ ሲቪል ሰዎች አስክሬን በክልሉ ልዩ ኃይሎች እና መደበኛ ፖሊሶች በጭነት መኪና ተሰብስቦ ወዳልታወቀ ቦታ እንደተወሰደና በጅምላ እንዲቀበሩ የተደረገ መሆኑን ጠቅሶ አስክሬን እንዲሰጣቸው ጥያቄ ያቀረቡ የሟች ቤተሰቦችም መከልከላቸውን እንዳረጋገጠ በሪፖርቱ ይፋ አድርጓል፡፡
የሟቾች አስክሬን ለምን ለቤተሰቦች እንዳልተሰጠና የተቀበሩበት ቦታ ለምን ለቤተሰቦች እንዳልተገለጸ ኢሰመኮ ላቀረበው ጥያቄ የክልሉ ፖሊስ በሰጠው ምላሽ አስክሬን ይሰጠን ብሎ ለፖሊስ ኮሚሽን ያመለከተ የከተማው ነዋሪ አለመኖሩን ገልጿል፡፡ “የሟቾች አስክሬን ለምን ለቤተሰቦች እንዳልተሰጠና የተቀበሩበት ቦታ ለምን ለቤተሰቦች እንዳልተገለጸ ኢሰመኮ ላቀረበው ጥያቄ የክልሉ ፖሊስ በሰጠው ምላሽ አስክሬን ይሰጠን ብሎ ለፖሊስ ኮሚሽን ያመለከተ የከተማው ነዋሪ አለመኖሩን የገለጸ ሲሆን፤ በአንጻሩ ተመሳሳይ ጥያቄ የቀረበለት የከተማው ማዘጋጃ ቤት “ፊዴራል ፖሊስን አነጋግሩ” የሚል ምላሽ ሰጥቷል። የፌዴራል ፖሊስ በበኩሉ አስክሬኖች ተሰብስበው የተቀበሩት በማዘጋጃ ቤት መሆኑን ገልጿል” ሲል ኢሰመኮ በሪፖርቱ ውስጥ ጽፏል።
የጋምቤላ ክልል ባለሥልጣናት “ወደ ከተማው የገቡት የኦነግ ሸኔ እና ጋነግ ታጣቂዎች የሲቪል ሰዎችን ልብስ ጨምሮ የተለያዩ በሥራ ላይ ያሉ እና የሌሉ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎችን መለዮ ልብሶች ለብሰው የነበረ በመሆኑ እና ውጊያው በከተማ ውስጥ በመከናወኑ የተለያዩ ብሔሮች ተወላጅ የሆኑ አስራ ሰባት ሲቪል ሰዎች መሞታቸውን” ገልፀዋል።
የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽንም አምስት ሲቪል ሰዎች በውጊያው ወቅት በኦነግ ሸኔ እና ጋነግ ሰኔ 7 ቀን 2014 ዓ.ም. መገደላቸውን፣ ከእነዚህ በተጨማሪ ሌሎች ሁለት ሲቪል ሰዎች መገደላቸውን፣ በየመንገዱ የነበሩ አስክሬኖች በከተማው ማዘጋጃ ቤት ተሰብስበው መቀበራቸውን፣እንዲሁም ዝርፊያ የተፈጸመ ስለመሆኑ የሚያሳዩ መረጃዎች እንዳሉት ነገር ግን ጥሰቶቹ የተፈጸሙበትን ሁኔታ እና የፈጻሚዎችን ማንነት በተመለከተ የተረጋገጠ ነገር እንደሌለ ለኢሰመኮ መግለፃቸውን ሪፖረቱ ያስረዳል፡፡
በመጨረሸም ኢሰመኮ የመብት ጥሰቶችን የፈጸሙ ሰዎችና ቡድኖችን ተጠያቂነት ለማረጋገጥ የሚደረጉ ጥረቶችን ለማገዝ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ፣ ተጎጂዎች ፍትሕ እና ተገቢውን የካሳ እና መልሶ መቋቋም ድጋፍ እንዲያገኙ የጠየቀ ሲሆን ተፈጻሚነቱንም የሚከታተል መሆኑንም አሳስቧል።
ሰኔ 7 ቀን በጋምቤላ ከተማ ከጠዋቱ 12፡30 ጀምሮ በ”ጠላት ጦር” እና በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች መካከል የተኩስ ልውውጥ እየተደረገ እንደነበር የጋምቤላ ክልል መንግስት ዋቢ አድርጎ አዲስ ስታንዳር መዘገቧ ይታሳል። የጋምቤላ ክልል መንግስት ባወጣው መግለጫ የጋምቤላ ነፃነት ግንባር (ጋነግ) እና መንግሥት ሸኔ ብሎ የሚጠራው የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት (ኦነሰ) ጋር በመቀናጀት በጋምቤላና በአካባቢው ተኩስ መክፈታቸውን አስታወቋል፡፡
የጋምቤላ ነፃነት ግንባር (ጋነግ) እና የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት (ኦነሰ) ቃል አቀባይ በበኩላቸው የጋምቤላ ዋና ከተማን ለመቆጣጠር በቅንጅት ዘመቻ መጀመራቸውን ገልፀው ነበር፡፡በግምቢና ደምቢ ዶሎ ከተሞች የኦነግ ሃይሎች ከመንግስት ሃይሎች ጋር እየተዋጉ መሆኑንም አክሎ አስታወቋል፡፡
የጋምቤላ ነፃነት ግንባር (ጋነግ) በፌስቡከ ገፁ ዘመቻው የብልጽግና መንግሥት ሰራዊት ተቋማት፣ የብልጽግና መንግስት አመራሮች እና ሰራዊት ላይ ትኩረት ያደረገ መሆኑን ገልፆ ማንኛውም ስቭል ማይበረሰብ የበራር ጥይቶች ሰለባ እንዳይሆን ከቤቱ እንዳይወጣ አሳስቧል፡፡ በተመሳሳይ የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት (ኦነሰ) አለምአቀፍ ቃል አቀባይ ኦዳአ ታርቢ “የጋምቤላ ነፃነት ግንባር እና የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት የተቀናጀ ዘመቻ በአሁኑ ወቅት በጋምቤላ ዋና ከተማ እየተካሄደ ነው” ብለው ነበር።
በወቅቱ የከተማው ነዋሪ ለአዲስ ስታንዳርድ እንደተናገሩት ከተማዋ በጋምቤላ ነጻ አውጪ ግንባር እና በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (ኦነሰ) ቁጥጥር ስር መዋሏን ገልጿል።
የክልሉ መንግስት “የመንግስት ሃይሎች ከፍተኛ ውጊያ ካደረጉ በኋላ የከተማዋን በከፊል ነፃ ማውጣት ተችሏል” ሲል ተጨማሪ መግለጫ ማውጣቱም ያታወሳል።አስ