ዜና፡ በደቡብ ክልል በ42 ወረዳዎች የኮሌራ ወረርሽኝ መከሰቱን እና አራት ሺ ታማሚዎች መኖራቸውን የአለም የጤና ድርጅት አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 22/2015 ዓ.ም፡- በኢትዮጵያ በነሃሴ ወር 2014 ዓ.ም የጀመረው የኮሌራ ወረርሽኝ በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ ሁኔታ በደቡብ ክልል በመዛመት ላይ እንደሚገኝ እና 42 የክልሉ ወረዳዎችም በወረርሽኙ መጠቃታቸውን የአለም የጤና ድርጅት አስታወቀ። በአሁኑ ወቅት በኮሌራ በሽታ የተያዙ ከአራት ሺ በላይ ሰዎች መኖራቸውንም ጠቁሟል።

የፌደራል መንግስቱ እና ለጋሽ ድርጅቶች ለወረርሽኙ ፈጣን እና የተቀናጀ ምላሽ ለመስጠት እየሰሩ መሆኑንንም የአለም የጤና ድርጅት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። ወረርሽኙ በተከሰተባቸው አከባቢዎች በለሞያዎች ማሰማራቱን የገለጸው የአለም የጤና ድርጅት ለማህበረሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች እየሰራ እንደሚገኝም አመላክቷል።

ወረርሽኙ በተከሰተባቸው አከባቢዎች የኮሌራ ማገገሚያ ማዕከላት መከፈታቸውንም የጠቆመው መግለጫው በማእከላቱ አስር እና ከዚያ በላይ ታማሚዎች በየቀኑ አገልግሎት እንደሚገኙ ገልጿል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች አስተባባሪ ኦቻ ይፋ ያደረገው ሪፖርት ሰባት ሚሊየን ኢትዮጵያውያን የኮሌራ ወረርሽኝ ሊያጠቃቸው ይችላል ሲል ስጋቱን መግለጹን መዘገባችን ይታወሳል።

ሀገራዊ የኮሌራ በሽታ መከላከያ ክትባት ዘመቻ በደቡብ ክልል ደቡብ ኦሞ ዞን በበናፀማይ ወረዳ ብራይሌ ከተማ በይፋ መጀመሩን የጤና ሚኒስትር ማስታወቁን በሌላ ዘገባ ሽፋን አግኝቷ። የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ ዘመቻውን ሲያስጀምሩ ባስተላለፉት መልእክት ባለፉት አመታት መከላከልን መሰረት ባደረገው የጤና ፖሊሲ በርካታ ውጤቶች መገኘታቸዉን አስታውቀው በተለይም የእናቶችና ህፃናትን ጤና ከማሻሻል፣ ተላላፊ በሽታዎችን ከመከላከልና መቆጣጠር ረገድ አመርቂ ውጤቶች ቢመዘገቡም ዛሬም ድረስ ኮሌራን ጨምሮ በወረርሽኝ መልክ የሚከሰቱ የጤና ችግሮችን ለመቅረፍ በርካታ ስራዎች ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል። አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.