በድርቁ የሞቱ ከብቶች ፤ ፎቶ- የሀመር ወረዳ ኮሙኒኬሽን
አዲስ አበባ፣ የካቲት 25/ 2015 ዓ.ም፡– በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል በደቡብ ኦሞ ዞን 6 ወረዳዎች በተከሰተ ድርቅ ከሶስት መቶ ሺህ ሰው በላይ ለረሀብ መጋለጡን የደቡብ ኦሞ ዞን የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ፅህፈት ቤት አስታወቀ።
የድርቁ መነሻ በባለፈው አመትም ሆነ በዚህ አመት ከፍተኛ የሆነ የዝናብ ስርጭት እጥረት በማጋጠሙ የደረሱ ሰብሎች በመቃጠላቸውና የእርሻ እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ተፅእኖ በማሳደሩ መሆኑን የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ዱባ ያራ አስታውቀዋል።
በዚህም ምክንያት በማሌ፣ በናፀማይ፣ ሐመር፣ ኛንጋቶም፣ ዳሰነችና ሳላማጎ ወረዳዎች ላይ ሶስት መቶ 37ሺህ 9መቶ 25 የማህበረሰብ ክፍሎች ለከፋ ረሀብ መጋለጣቸውን ጠቁመዋል።
ሁለት ነጥብ አራት ሚልየን የሚሆኑት እንስሳትም የመኖ እጥረት እንዳጋጠማቸው ገልጸው ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው እንስሳት ለሞት መዳረጋቸውን አሳውቀዋል። በዝናቡ እጥረት ምክንያትም የማሌ፣ የበናፀማይና የሐመር ወረዳዎችን አካሎ ሰፊ ሽፋን የሚሰጠው የወይጦ ወንዝ ሙሉ በሙሉ በመድረቁ መሆኑን የጠቆሙት ሀላፊው የኦሞ ወንዝም መጠን በመቀነሱ ለችግሩ አይነተኛ ምክንያት እንደሆነ አመላክተዋል።
የዞኑ መንግስት እና ግብረሰናይ ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት ከፍተኛ የሆነ ጉዳት ያለባቸው ሰዎችን በመለየት የመጀመርያ ዙር የምግብ እህል እርዳታ መደረጉን የገለጹት ሃላፊው አቶ ዱባ ያራ በቀጣይም ለሁሉም ወጥ በሆነ መልኩ ተደራሽ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል። ፌደራል መንግስቱን ጨምሮ ሁሉም የመንግስት አካላት፣ ግብረሰናይ ድርጅቶችና በውጭ የሚኖሩ አገር ወዳድ ዜጎች ለዘላቂ መፍትሔው ርብርብ እንዲያደርጉ ሲሉ ሃላፊው ጥሪ ማቅረባቸውን ከዞኑ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ማህበራዊ ሚዲያ የፌስቡክ ገጽ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።
በተመሳሳይ በደቡብ ኦሞ ዞን ስር የምትገኘው የሐመር ወረዳ ኮሙዪኒኬሽን ቢሮ በበኩሉ በወረዳው በተከሰተው ድርቅ ሳቢያ የአርብቶ አደሩ የኑሮ መሠረት የሆኑት የቀንድ ከብቶቹ በየጫካና ጥሻዎቹ ውስጥ በተኙበት እየሞቱ እንደሚገኙ አስታውቋል።
በወረዳው ለተከታታይ አራት ዓመት በቂ ዝናብ ባለመጣሉ ድርቁ መከሰቱን የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ ፎራ ጋርሾ ገልጸዋል ያለው መረጃው አርብቶ አደሩ የግጦሽ አማራጮችን ለመፈለግ ወደ አጎራባች ወረዳዎች እንስሳቱን በሚያንቀሳቅስበት ወቅትም አላስፈላጊ ግጭቶች እንደሚፈጠሩ መጠቆማቸውን አካቷል።
“አሁን ላይ በሐመር ድርቁ ዕለት በዕለት የአርብቶ አደሩ መተዳደሪያ የሆኑ የቁም እንስሳትን በከፍተኛ ሁኔታ እየጨረሰ ነው። ውኃ የለም፤ ሣር የለም። አርብቶ አደሩ የእንስሳት ተዋጽዖ በመመገብ ነው የሚኖረው። ዝናብ የለም በዚህ ምክንያት ብዙ ከብቶች እየሞቱ ነው። ሰውም በጣም በከፍተኛ ሁኔታ በረሐብ እየተሰቃየ ነው” ሲል ቢሮው ገልጧል፡፡አስ