በብሩክ አለሙ @Birukalemu21
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 24/ 2014 ዓ.ም፡- በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል (ደ/ብ/ብ/ህ/ክ/) የ ገንዲ/የእንቅልፍ በሽታ/ (Human Africa Trypanosomiasis) የተባለና የመግደል አቅም ያለው አዲስ በሽታ መከሰቱን የደቡብ ክልል ጤና ቢሮ የሕብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት አስታውቀ፡፡
የገንዲ በሽታ /እንቅልፍ በሽታ (Trypanosomiasis) በቆላ ዝንብ አማካይነት የሚተላለፍና እንስሳትና ሰውን የሚያጠቃ በሽታ ሲሆን በጋሞ ዞን በቁጫ አልፋ ወረዳ የኦሞ ወንዝ ሸጥ ከሆኑ ቀበሌያት ወደ ሰላምበር መጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ለህክምና በመጡ ታካሚዎች ላይ በተወሰደ ናሙና አማካኝነት በሽታው መገኘቱ ተረጋግጧል ተብሏል፡፡
አፋጣኝ የህክምና እርዳታ ካልተገኘ የሰው ልጆችን ጤና እጅግ ፈታኝ እንደሚያደርግ እና በቂ ህክምና ባላገኙ በሽተኞች ላይ የመግደል አቅሙ እስከ 100% ሊደርስ እንደሚችል የክልሉ የሕብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት አስታውቋል፡፡
በሽታው ከእናት ወደ ልጅ ሊተላለፍ የሚችል ሲሆን በበሽታዉ የተጠቃች ዝንብ ከተነከሱ እንዲሁም በግብረ ስጋ ግኙኝነት የሚተላለፍ መሆኑን ኢኒስቲትዩ አስታውቋል፡፡ ትኩሳት፣ ራስ ምታት፣ የመገጣጠሚያና ጡንቻ ህመም፣ ማሳከክ፣ በትክክል አለማሰብና የመረበሽ፣ እንቅልፍ እንቅፍ ማለት እና የእጥዎች ማበጥ የበሽታው ምልክቶች መሆናቸውንም አክሎ ገልጿል፡፡
የቆላ ዝንቦች በሚገኙባቸው ቦታዎች ትራፕ (ወጥመድ) በመትከል፣ በኬሚካል የተቀባ ታርጌት የቆላ ዝንቦች በሚገኙባቸው ቦታዎች በመስቀል፣ የመሬት ለመሬት ኬሚካል ርጭት በማካሄድ፣ የቆላ ዝንቦች በሚገኙባቸው አካባቢ በሚሰማሩ እንስሳት ጀርባ ላይ ኬሚካል በመቀባት፣ በአይሮፕላን የኬሚካል ርጭት በማካሄድ፣ በበሽታው የተጠቁ ሰዎች በቂ ህክምና እንዲያገኙ ማድረጎ እና በላቦራቶሪ የሚመረቱ መካን ወንድ የቆላ ዝንቦችን በመጠቀም የቆላ ዝንቦቾን ማጥፋት በሽታውን መቆጣጠር የሚያስችሉ ዘዴዎች መሆናቸውን ኢኒስቲትዩቱ አስታውቋል፡፡
ኢኒስቲትዩቱ በክልሉ በየትኛውም አካባቢዎች መሰል የህመም ምልክቶች ክስተት ዙሪያ በህረተሰቡ ዘንድ ግንዛቤ እየተፈጠረ መሄድ ስላለበት እና በተለይ አሁን ክስተቱ በተፈጠረባቸው አከባቢዎች ጋር አጎራባች የሆኑና አና በማህበራዊ ትስስር የሚገናኙ ሁሉም ቀበሌዎች ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ በየአከባቢው ባሉ የጤና መዋቅር በአስቸኳይ ሪፖርት እንዲደረግ ጥሪ አቅርቧል፡፡
በአገራችን ትኩረት የሚሹ አሩራማ በሽታዎች ከመከላከልና ከመቆጣጠር አንፃር ከዓለም ጤና ድርጅት እና ከተለያዩ አጋር ድርጅቶች ድጋፍ የፌዴራል ጤና ሚኒስቴር ከኢትዮጲያ ህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት እና ከጤና ቢሮ ጋር በመተባበር በተለያዩ የጤና ፕሮግራሞች በተቋማትና በማህበረሰብ አቀፍ እየተከናወኑ እንደሚገኙ ተነግሯል፡፡
በሽታውን የሚያስተላልፈው የቆላ ዝንብ ከሠሀራ በታች ባሉ 37 የአፍርካ አገሮች ተሰራጭቶ የሚገኝ ሲሆን በቆላ ዝንቦች አማካይነት የሚተላለፈው የገንዲ በሽታ ከፍተኛ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖ በማድረስ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስ በሽታ ነው፡፡ በአፍሪካ 31 ዓይነት የቆላ ዝንብ ዝርያዎች የሚገኙ ሲሆን ከእነዚህም አምስት የቆላ ዝንብ ዝርያዎች በሀገራችን ኢትዮጵያ ይገኛሉ፡፡ በአፍሪካ 60 ሚሊዮን የሚገመት ህዝብ ለዚህ በሽታ የተጋለጠ እንደሆነ የዓለም ጤና ድርጅት ሪፖርት ማድረጉን ከደ/ብ/ብ/ህ/ክ/ ጤና ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
የደ/ብ/ብ/ህ/ክ/ መንግስት ጤና ቢሮ የሕብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት የህዝብ ግኑኝነት ሃላፊን ለተጨማሪ መረጃ ለማናገር ያደርግነው ሙከራ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡አስ