ዜና፡ የቀድሞ የኢህአዴግ ባለስልጣን የነበሩት አቶ በረከት ስምዖን በአሞክሮ ከእስር ተፈቱ፤ ቤተሰቦቻቸው አዲስ አበባ ዛሬ ይገባሉ ብለው  እየጠበቋቸው መሆኑን አስታውቀዋል

አዲስ አበባ፣ ጥር 17/2015 ዓ.ም፡-  የቀደሞ የብአዴን መስራች አባል እና የኢህአዴግ ባለስልጣን የነበሩት አቶ በረከት ስምዖን  ታስረው ከነበረበት የባህርዳር እስር ቤት የአሞክሮ ግዜያቸውን በማጠናቀቃቸው በዛሬው እለት ከእስር መፈታታቸውን ጠበቃቸው ህይወት ሊላይ ለአዲስ ስታንዳርድ አስታውቀዋል።

የአቶ በረከትን መፈታታቸውን ያረጋገጡልን አንድ የቅርብ ቤተሰብ አባል እንደገለፁት ቤተሰቦቻቸው ዛሬ አዲስ አበባ  ይገባሉ ብለው  እየጠበቋቸው ነው ብለዋል፡፡

በክልሉ ህግ መሰረት የእስር ግዜያቸውን አንድ ሶስተኛ ባጠናቀቁበት ወቅት ማለትም ከወራት በፊት ሊፈቱ ይገባቸው እንደነበር የገለጹልን የህግ ጠበቃቸው ህይወት ሊላይ ይህን እንዲያገኙ ባይፈቀድላቸውም በዛሬው እለት የአሞክሮ ግዜያቸውን በማጠናቀቃቸው መፈታታቸው አስታውቀዋል።

አቶ በረከት ስምዖን ከቀድሞ የጥረት ኮርፖሬሽን የስራ ባልደረባቸው አቶ ታደሰ ካሳ ጋር ለእስር የተዳረጉት በታህሳስ 23 2019 ዓ/ም ከኮርፖሬሽኑ ጋር በተያያዘ በሙስና እና ብልሹ አስተዳደር ወንጀል መሆኑ ይታወሳል። ጥረት ኮርፖሬሽን በ1995 በዛኔው ብአዴን የተቋቋመ ነው። በሁለቱም ባለስልጣናት ላይ የተመሰረተው ክስ በጥረት ኮርፖሬሽን  በሃላፊነት ላይ እያሉ ሁለት ነጥብ ሁለት ቢሊየን ብር ለብክትነት ዳርገዋል በሚል ነበር።

በወቅቱ ክስ ተመስርቶባቸው የነበሩት ሶስተኛ ተከሳሽ አቶ ዳንኤል ግዛው የተባሉ ነጋዴ ነጻ ተብለው መሰናበታቸው ይታወሳል።  አቶ በረከት እና አቶ ታደሰ የተመሰረተባቸውን ክስ እስከ ግንቦት 2020 ሲከላከሉ የቆዩ ቢሆኑም አቶ በረከት የስድስት አመት እስር እና አስር ሺ ብር ቅጣት አቶ ታደሰ ደግሞ ስምንት አመት እና አስራ አምስት ሺ ብር ቅጣት ብይን ተሰጥቶባቸዋል። በወቅቱ ይግባኝ ጠይቀው የነበረ ቢሆንም ተቀባየነት ባለማግኘቱ ብይኑ ጸንቶ አቶ በረከት የእስር ግዜያቸውን በአመክሮ አጠናቀው ተፈተዋል።

ለእስር ከመዳረጋቸው በፊት (ዳራ)

አቶ በረከት ላይ የሙስና ወንጀል ክስ ከመመስረቱ በፊት ከምስረታው ጀምሮ በአመራርነት ካገለገሉበት ብአዴን ጋር አለመስማማት ፈጥረው ነበር። ወቅቱም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ወደ ስልጣን በመጡበት 2018 ጥቂት ወራት በኋላ ነው። በዚያኑ አመት ነሐሴ ወር ላይ የፓርቲያቸው ስራ አስፈጻሚ አቶ በረከትን እና አቶ ታደሰን ከማእከላዊ ኮሚቴ አባልነታቸው አግዷቸዋል። በሁለቱም ላይ እግድ ከመጣሉ አስቀድሞ ብአዴን የለውጡን አጀንዳ ለማስኬድ ብቁ ካልሆኑ አመራሮች ጋር መቀጠል እንደማይችል የሚያትት መግለጫ አውጥቷል።

የህወሓት ታማኝ አገልጋይ ናቸው የሚል ሃሜት በአቶ በረከት ላይ መነዛት የተጀመረው ቀደም ብሎ በሰኔ 2018 ነበር። ሃሜቱ በከፍተኛ ደረጃ በተነዛ ከወር በኋላ ነሐሴ ላይ በምስራቅ ጎጃም በደብረማርቆስ ከተማ በሚገኝ ሆቴል ላይ ከአቶ በረከት ጋር በተያያዘ ብጥብጥ ተነስቶ ነበር። በፌደራል ፖሊስ እና ሆቴሉን በከበቡ ነውጠኞች መካከል ለተፈጠረው ብጥብጥ ዋነኛ ምክንያት በሆቴሉ አቶ በረከት እና የወቅቱ የክልሉ ጠቅላይ አቃቤ ህግ የነበሩትና በ2019 የተገደሉት  ምግባሩ ከበደ ከከተማው ታዋቂ ሰዎች ጋር ሚስጥራዊ ስብሰባ እያካሄዱ ነው የሚል አሉባልታ በመናፈሱ ነበር። አቶ በረከት የሚገለገሉባት መኪናነች በሚል በሆቴሉ የነበረች ተሽከርካሪ በነውጠኞቹ ተቃጥላለች። ሆቴሉም ከፍተኛ ጉዳት አስተናግዷል።

አቶ በረከት ለሁለት እሰርት አመታት ከኢህአዴግ ከፍተኛ ባለስልጣን ሁነው ከማገልገላቸው ባሻገር የድርጅቱ ርዕዮተ አለም የፖለቲካ አጀንዳ መሪ ተደርገው ይወሰዳሉ። የቀድሞ የኢህአዴግ ሊቀመንበር እና የኢፊድሪ ጠሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ የቅርብ አጋር ተደርገው ይቆጠራሉ። ከኢህአዴግ ከፍተኛ የሃላፊነት ቦታወች በተጨማሪ የኢንፎርሜሽን ሚንስትርነት እና የኮሚኒኬሽን ሃላፊ ሁነውም ሰርተዋል። በአቶ ሃማርያም ደሳለኝ የጠሚኒስትርነት ዘመን የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል ምክትል ዳይሬክተር ሁነው አገልግለዋል።አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.