ዜና፡ በወልቂጤ ከተማ የንፁህ ውሃ ችግር እንዲፈታላቸው ጄሪካን ይዘው ሰላማዊ ሰልፍ በወጡ ሰዎች ላይ የፀጥታ ሃይሎች በከፈቱት ተኩስ 6 ሰዎች ሲሞቱ ከ15 ሰዎች በላይ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል

በብሩክ አለሙ @Birukalemu21

አዲስ አበባ፣ የካቲት 9/ 2015 ዓ.ም፡- በወልቂጤ ከተማ በትላንትናው እለት በንፁህ ውሃ እጥረት ችግር ምክኒያት ጄሪካን ይዘው  ሰላማዊ ሰልፍ በወጡ የከተማዋ ነዋሪዎች ላይ የፀጥታ ሃይሎች በከፈቱት ተኩስ 6 ሰዎች ሲሞቱ ከ15 ሰዎች በላይ ላይ ከፍተኛ ጉዳት  መድረሱን የከተማዋ ነዋሪዎች ለአዲስ ስታንዳርድ ገለፁ፡፡

ለአመታት በውሃ እጠረት ሲቸገር የነበረ የከተማዋ ነዋሪ ችግሩ እንዲቀረፍ ጄሪካን ይዘው ሰላማዊ ሰላፍ በመውጣታቸው ብቻ በልዩ ሀይል ተኩስ ተከፍቶባቸው 6 ሰው የተገደሉ ሲሆን 15 ሰው ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሰዋል ሲል የከተማዋ ነዋሪ አቡበከር ከማል ለአዲስ ስታነዳርድ ተናግረዋል፡፡ በህክምና ላይ ያሉት በአስጊ ሁኔታ ውስጥ በመሆናቸው የሟቹቹ ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል ገልፀዋል፡፡

በክስተቱም የተነሳ መህበረሰቡ ላይ የደረሰው የስነ ልቦና ጫና ቀላል የሚባል አይደለም የሚሉት አቡበከር የፀጥታ ሀይሎች ህዝቡን እያሳደዱ አስከፊ ጥቃት መፈፀማቸውን ገልፀዋል፡፡

አክለውም ህብረተሰቡ መብቱን በመጠየቁ እንደ ወንጀለኛ ጥቃት ተከፍቶበት ለሞት እና ለከፍተኛ ጉዳት ተዳርጓል ብለዋል፡፡

“መጀመሪያ ህብረተሰቡ ተሰባስቦ ወደ ውሃ ልማት ጽ/ቤተ ነበር ሰላማዊ ሰልፉን ያደረገው፡፡ ምላሽ ሲያጣ በመቀጠልም ወደ ከተማ አስተዳደሩ ቢያመራም ልዩ ሃይሎች መጥተው ተኩስ ከፈቱባቸው፡፡ ተኩሱን በመፍራት ሲሰሹ እየተከተሉ በማጥቃት 6 ሰዎችን ገድለው ከ 15 በላይ ሰዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት አደረሱ” በማለት አቡበከር አስረድተዋል፡፡

በአሁኑ ሰዓትም በወልቂጤ ከተማ የንግድ ስርዓቱ መቆሙንና የመንግስትና የግል ተቋማት ዝግ መሆናቸውን አክለው ገልፀዋል፡፡

ሌላኛው የከተማዋ ነዋሪ የሆኑት ሀይደር ሙራድ “በወልቂጤ ከተማ በተለይ ላላፉት ሶስት ወራቶች ከፍተኛ የውሃ እጥረት በመኖሩ የከተማዋ እናቶች እና ወጣቶቸ ጃሪካን ይዘው ችግሩ እንዲፈታ በሰላማዊ መንገድ ጥያቄያቸውን እያሰሙ እያሉ የፀጥታ ሃይሎች ያለርህራሄ እናቶቱ ላይ እና ወጣቶቹ ላይ በመቶኮስ 6 ሰዎችን ገድለዋል” ሲሉ ለአዲስ ስታንዳርድ ገልፀዋል፡፡ ከ 15 ሰዎች በላይ የሚሆኑ በአሁኑ ሰዓት የፅኑ ህሙማን ክፍል ውስጥ እንደሚገኙም ገልፀዋል፡፡

ሟቾቹ ምንም የማያውቁ እናቶቻቸውን ተከትለው የወጡ ልጆች መሆናቸውን የሚናገሩት ሀይደር በህክምና ላይ ያሉትም አስጊ ሁኔታ ላይ በመሆናቸው ቁጥሩ ሊጨምር እንደሚችል ተናግረዋል፡፡

ሰላማዊ ሰልፍ የወጣ ማህበረሰብን በሰላም እንዲገባ ማድረግ እየተቻለ በመሳርያ እያሰደዱ መግደል አግባብነት የሌለው ተግባር መሆኑን ጠቅሰው በዓሁኑ ወቅት ማህበረሰቡ ቤቱን ዘግቶ ሀዘን ላይ ነው ያለው ብለዋለ፡፡

ጨምረው በአሁኑ ሰዓትም የፀጥታ ሀይሎቹ ዱካን የተጣለበት አካባቢ በመሄድ የሟቾች ቤተሰቦች ሀዘን ላይ እንዳይቀመጡ፣ ሀዘንተኛ እንዳይመጣ  ለማድረግ ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ ሲሉ አክለው ገልፀዋል፡፡

በጉራጌ ዞን ከህዳር 16 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ በተደረጃ ኮማንድ ፖስት እንዲመራ መወሰኑ ይታወሳል፡፡ የደቡብ ክልል ሠላምና ፀጥታ ቢሮ ሀላፊ አቶ አለማየሁ ባውዲ በዞኑ እየተፈጠረ ያለው ችግር በመደበኛ አሰራር ለማስተዳደር አስቸጋሪ ሁኔታዎች በመፈጠራቸው የፌድራል ፖሊስ፣ የክልሉ ልዩ ሃይል እና ሌሎችም የፀጥታ አካላትን ጨምሮ  በቅንጅትና በተደራጀ መንገድ አካባቢው ውስጥ እየተፈጠረ ያለውነን የፀጥታ ችግር ያስተዳድራል ብለዋል፡፡

በወልቂጤ ከተማ ኮማንድ ፖሰቱን እና ክላስተርን በመቃወም በተደጋጋሚ ስራ የማቆም አድማ ሲደረግ ቆይቷል፡፡ በቅርቡም ጥር 29፣2015 ዓ.ም. በከተማዋ ለአራተኛ ጊዜ ስራ የማቆም አድማ መደረጉም ይታወቃል፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ የጉራጌ ዞን የፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ያእቆብን በስልክ ለማነጋገር ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም፡፡ አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.