አዲስ አበባ፣ ሰኔ 12/2015 ዓ.ም፡- በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የሚገኙ የ6 ዞኖች (የጋሞ፣ ወላይታ፣ ጎፋ፣ ጌዴኦ፣ ኮንሶ እና የደቡብ ኦሞ ዞኖች) እና የ5 ልዩ ወረዳዎች(የቡርጂ፣ የአማሮ፣ የደራሼ፣ የባስኬቶ እና የአሌ ) በአንድ ክልል ለማደራጀት ለመወሰን ይረዳ ዘንድ በወላይታ ዞን የዳግም ህዝበ ውሳኔ የድምጽ አሰጣጥ ሥነ ሥርዓት ዛሬ ሰኔ 12 ከማለዳ 12፡00 ጀምሮ እየተከናወነ ከጠዋት 12፡00 ሰዓት እስከ 6፡00 ሰዓት 370,552 መራጭ ድምፅ መስጠታቸውን ምርጫ ቦርድ አስታወቀ፡፡
በ1812 የምርጫ ጣቢያዎች የተሟላ የምርጫ ቁሳቁሶች መድረሳቸውን የገለፀው ቦርዱ የድምፅ መስጠት ሂደት ቦርዱ ለሶስት የሀገር ውስጥ ተቋማት የታዛቢነት እውቅና ሰጥቶ በዞኑ የተለያዩ ጣቢያዎች ላይ 214 ታዛቢዎች ተሰማርተዋል ብሏል።
ቦርዱ የድጋሚ ህዝበ ውሳኔውን የሚያከናውኑ የምርጫ አስፈፃሚዎችን በተለያየ መንገድ መመልመሉን በመግለፅ ከአዲስ አበባ 5215 የምርጫ አስፈፃሚዎች እና ከወላይታ 3845 የምርጫ አስፈፃሚዎች አሳትፊያለው ሲል ገልጧል።
በዛሬው እለት ሁሉም አስፈፃሚዎች በስራ ላይ ተሰማርተው መራጮችን በማስተናገድ ላይ የሚገኙ ሲሆን አንድ አንድ ሰልፎች የበዙባቸው ጣቢያዎች ላይ ቦርዱ አሰልጥኖ በተጠባባቂነት የያዛቸውን አስፈፃሚዎችን አሰማርቷል።
የድምፅ መስጠት ሂደቱ ከተጀመረ በኋላ በርከት ያሉ መራጮች ከተሠጣቸው 6 ወር ያልሞላው መታወቂያ ሆኖ ተገኝቷል። ነገር ግን የቦርዱ መመሪያ አንድ ዜጋ ድምፅ መስጠት የሚችለው በመኖርያ ስፍራው ቢያንስ ለስድስት ወር እና ከዚያ በላይ መኖሩ መረጋገጥ እንዳለበት ተጠቅሷል። ስለዚህ እነዚህ መራጮች ከያዙት የነዋሪነት መታወቂያ በተጨማሪ ነዋሪነታቸውን የሚያረጋግጡበት የሶስት ሰዎች ምስክርነት ወይም ሌሎች የሠነድ ማስረጃዎችን በማቅረብ ድምፅ እንዲሰጡ ተደርጓል ብሏል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በደ/ብ/ብ/ሕ ክልል በሚገኙ ስድስት ዞኖች እና አምስት ልዩ ወረዳዎች ላይ ለሚያከሄደው ሕዝበ ውሣኔ፣ በዎላይታ እና በጎፋ ዞኖች በሚገኙ አንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች ላይ መሠረታዊ የሆኑ የሕግ ጥሠቶች በመፈፀሙ የተደረገው ምዝገባ እንዲሠረዝ ማድረጉ ይታወሳል፡፡
ምርጫ ቦርድ ለሚያካሂደው ሕዝበ ውሳኔ ከታህሳስ 11 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ እያካሄደ ባለው የመራጮች የምዝገባ ሂደት ላይ በዎላይታ እና በጎፋ ዞኖች ስር በሚገኙ በአስር ምርጫ ጣቢያዎች ላይ በተፈፀሙ የህግ ጥሰቶች ምክኒያት የመራጮች ምዝገባ ሂደቱ ሙሉ በሙሉ እንዲቆም ማድረጉ ይታወሳል፡፡
በወቅቱ ቦርዱ እንዳስታወቀው በዎላይታ ዞን ዱቦ ምርጫ ጣቢያ አቶ መሰለ ኤሊያስ ከሚባል ግለሰብ ስም ዝርዝር በመቀበል በመራጮች መዝገብ ላይ የመመዝገብ የህግ ጥሰት ተፈፅሟል፣ በተጨማሪም የቦርዱ ሠራተኛ ላልሆነ አቶ ወልዴ ወራጆ ለተባለ ግለሰብ ቁልፍ በመስጠት ምዝገባውን እንዲያከናውኑ ማድረግ እንዲሁም በዞኑ ዶላ ምርጫ ጣቢያ ሦስት ንዑስ ጣቢያ ውስጥ አቶ አርጃ አሊሶ ከሚባል ግለሰብ ስም ዝርዝር በመቀበል በመራጮች መዝገብ ላይ የመመዝገብ የህግ ጥሰቶች በመፈፀማቸው ምርጫው ተሰርዟል፡፡አስ