አዲስ አበባ፣ የካቲት 17/ 2015 ዓ.ም፡- አስራ ሁለት የሚሆኑ በኦሮምያ ክልል የሚንቀሳቀሱ መንግስታዊ ያልሆኑ የእርዳታ ድርጅቶች በክልሉ በተከሰተው ቀውስ ከ14 ሚሊየን በላይ የክልሉ ነዋሪዎች በድርቅ እና ግጭቶች ሳቢያ አስቸኳይ የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው በመጥቀስ ባለድርሻ አካላት ልዩ ትኩረት በመስጠት የጋራ የትብብር እንዲያደርጉ ጥሪ አቀረቡ።
“የኦሮምያ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የሰብአዊነት ጥምረት” (ONHA) በሚል መጠሪያ መግለጫ ያወጡት ድርጅቶቹ አስቸኳይ የምግብ እርዳታ ከሚያስፈልጋቸው ውስጥ ሶስት ነጥን አራት ሚሊየን የሚሆኑት ከቀያቸው የተፈናቀሉ መሆናቸውንም አመላክተዋል።
በቦረና የተከሰተውን አስመልክቶ መግለጫው ባመላከተው መረጃ መሰረት በትንሹ አርባ ስድስት በመቶ የሚሆነው የአከባቢው እንስሳት የሞቱ ሲሆን አብዘሃኛው ቤተሰብ የነበሩትን የቤት እንስሳት ማጣቱን ገልጿል። በክልሉ በተለይም በቦረና ያለው አጠቃላይ ሁኔታ ለአከባቢው ነዋሪዎች በከፍተኛ ደረጃ አስጊ መሆኑን የጠቆመው የጥምረቱ መግለጫ በቦረና ታሪክ የዚህ አይነት ድርቅ አጋጥሞ አያውቅም ብሏል።
በክልሉ የሚገኙ ከቀያቸው የተፈናቀሉ ስደተኞች ምግብ፣ መጠለያ፣ የጤና አገልግሎት፣ ትምህርት እና ንጽህና መጠበቂያ ሊሟላላቸው እንደሚገባ አሳስቧል። በክልሉ 3 ነጥብ 7 ሚሊየን ህዝብ አስቸኳይ የመጠጥ ውሃ ድጋፍ ሊደረግለት እንደሚገባ አስታውቋል።
በማከልም ቁጥራቸው ቀላል የማይባል በእድሜ የገፉ፣ አጥቢ እናቶች እና እድሜያቸው ከአምስት አመት በታች የሆኑ ህጻናት ከፍተኛ የተመጣጠነ የምግብ እጥረት እንደታየባቸው ጠቁሟል። በርካታ የአከባቢው ነዋሪ መካከለኛ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት እንደሚታይባቸው ያስታወቀው መግለጫው በአጭር ግዜ ውስጥ ወደ ከፍተኛ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ሊያድግ እንደሚችልም አሳስቧል፡፡
የኦሮምያ ልዩ ዞንን ጨምሮ በተራዘመው ድርቅ እና ግጭት ሳቢያ የተጎዱ የክልሉ ነዋሪዎች በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ በመጦቆም አስቸኳይ የሰብዓዊ እርዳታ እንዲደረግላቸው አሳስቧል። አክሎም የሰብአዊ ድጋፍ ለሚያደርጉ አጋሮቹ ባስተላለፈው መልዕክት በክልሉ የተከሰተውን ሰብአዊ ቀውስ በጥልቀት እንዲመረምሩት እና የተፈጠረው ሰብአዊ ቀውስ የሚመጥን ፈንድ እንዲመድቡ ጠይቋል።አስ