ዜና፡ በአንዋር መስጊድ በተነሳ ረብሻ ሶስት ሰዎች መሞታቸውን እና በ63 የጸጥታ አባላት ላይ ጉዳት መድረሱን የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ-ኃይል አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 26/2015 ዓ.ም፡- የኢትዮጵያ የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ-ኃይል ግንቦት 25 ቀን 2015 በሰጠው መግለጫ በአዲስ አበባ አንዋር መስጊድ በተነሳ ረብሻ የሶስት ሰዎች ህይዎት ማለፉን እና በ63 የፖሊስ አመራር እና አባላት ላይ ቀላል እና ከባድ የአካል ጉዳት መድረሱን አስታውቋል። በንብረት ላይም እስከ አሁን ግምቱ ያልተወቀ ኪሳራ መድረሱን ግብረሃይሉ በመግለጫው አመላክቷል።

በአዲስ አበባ በሁሉም ክፍለ ከተሞች በሚገኙ መስጅዶች የተካሄደው የጁምአ ሶላት በሰላም መጠናቀቁን ያስታወቀው መግለጫው ሁከት እና ብጥብጥ የተፈጠረው በአንዋር መስጊድ እንደነበር ገልጿል። በአንዋር መስጊድም ቢሆን የጁምዓ ሶላት በሰላም ተጠናቆ ህዝብ ሙስሊሙ እየተመለሰ ባለበት ሁኔታ ችግሩ እንደተፈጠረ አመላክቷል።

ሀይማኖትን ሽፋን በማድረግ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለማፍረስ የሚንቀሳቀሱ የሴራ ቡድኖች ሲል ግብረ ሀይሉ የገለጻቸው አካላት ለችግሩ መፈጠር ተጠያቂ መሆናቸውን ጠቁሟል።

ፀረ-ሰላም ኃይሎች የእምነቱ ተከታዮች በህጋዊ መንገድ ያቀረቡትን ጥያቄ በመጥለፍ የራሳቸውን እኩይ ዓላማ ለማሳካት ረብሻውን ወደ ሌሎች አካባቢዎች ለማዛመት ያደረጉት ጥረት የፀጥታ ኃይሉ፣ ህዝበ ሙስሊሙ እና የሀይማኖቱ አባቶች በጋራ በመሆን ባደረጉት ርብርብ መቆጣጠር ተችሏል ሲል መግለጫው አካቷል።

ግብረ-ኃይሉ የከተማውን ብሎም የሀገሪቱን ሠላምና ደህንነት ለማስጠበቅ የጀመረውን ሥራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል የገለጸ ሲሆን የደረሰውን አጠቃላይ ጉዳት እና በሁከቱ የተሳተፉ ኃይሎች ላይ የጀመረውን ምርመራ ሲያጠናቅቅ ውጤቱን ለህዝቡ ይፋ እንደሚያደርግ ገልጿል።

በህዝበ ሙስሊሙ የሚያነሳውን ማንኛውንም ጥያቄ በህግ አግባብ በሰላማዊ መንገድ ማስተናገድ የሚቻልበት ሥርዓት መኖሩን የገለጸው የግብረ ሃይሉ መግለጫ ህዝበ ሙስሊሙ የፀጥታ አካላት የከተማውን ሰላምና ደህንነት ለመጠበቅ የሚያደርጉትን ጥረት እንዲደግፍ ጠይቋል። አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.