አዲስ አበባ፣ ግንቦት 1/2015 ዓ.ም፡- የፌደራል መንግስት በአማራ ክልል ወታደራዊ ዘመቻ እያካሄደ እና ነገሮችን ለመቆጣጠር ጥረት እያደረገ ቢሆንም ከግንቦት አጋማሽ ጀምሮ እየተባባሰ ሊቀጥል እንደሚችል ላለፉት 55 አመታት በሀገራት ጸጥታ ስጋት ዙሪያ በመስራት የሚታወቀው ክራይስስ24 የተሰኘ ተቋም ጥናት አመላከተ። ተቋሙ በድረገጹ እንዳስነበበው ከሆነ የፌደራል መንግስት የፋኖ አባላትን እና የአከባቢውን ሚሊሻዎች ትጥቅ ለማስፈታት እና በሀገሪቱ መደበኛ የጸጥታ መዋቅር ለማካተት የሚያደርገው ጥረት ውጥረት መፍጠሩን አስታውቆ ውጥረቱ እየጨመረ መቀጠሉ የማይቀር ነው ሲል ገልጿል።
በዝቅተኛ ደረጃ የሚመደብ ግጭት እና ብጥብጥ በክልሉ መከሰቱ ባለስልጣናቱ የተለያዩ ገደቦችን እንዲጥሉ ማስገደዱን ያወሳው ተቋሙ ጎንደርን ጨምሮ በተለያዩ የአማራ ክልል ከተሞች የመሰብሰብ እና መንቀሳቀስ ያካተተ በርካታ እግዶች መጣላቸውን አመላክቷል።
የፋኖ አባላት እና የክልሉ ሚሊሻ አባላት መሳሪያ የማያስረክቡ ከሆነ ወደ ውጊያ መግባታቸው የማይቀር ይሆናል ሲል ትንበያውን አስቀምጧል። ባህርዳር፣ ጎንደር፣ ደሴ፣ ሞጣ፣ እና ኮምቦልቻ ከተሞችን ጨምሮ የፌደራል መንግስቱ በአማራ ክልል ዋና ዋና ከተሞች በቀጣይ ቀናት ብዙ ቁጥር ያለው ወታደራዊ ሀይል ማስፈሩ የማይቀር ነው ሲል ገልጿል። ወታደራዊ ሀይሉ በከተሞቹ የፍተሻ ኬላ ማቋቋም፣ የስአት እላፊ መጣል እና የፓትሮል ስራዎችንም መስራቱ አይቀሬ ነው ሲል ጠቁሟል። የጸጥታ እና ደህንነት ዘመቻወች ማለትም የጉዞ ክልከላ፣ ግዜያዊ የየብስ ትራንስፖርት ማቋረጥ እና የኢንተርኔት መቆራረጥ በቀጣይ ቀናት መሰራታቸው አይቀሬ መሆኑንም አስታውቋል።
በተያያዘ ዜና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የ2015 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት የስራ አፈጻጸም ሪፖርቱን ለፓርላማው የዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረበበት ወቅት በአማራ ክልል በርካታ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች መስተዋላቸውን ገልጿል። ኮሚሽኑ የሚያቀርባቸው ምክረ ሐሳቦች በመንግሥት አስፈጻሚ አካላት ተግባራዊነታቸው እንዲረጋገጥ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ልዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ሲል አሳስቧል።
ዋና ኮሚሽነሩ በሪፖርታቸው “በአማራ ክልል እየተካሄደ ያለው ወታደራዊ እንቅስቃሴና የሰብአዊ መብቶች እንደምታው፣ የዘፈቀደ እስርና በእስር ወቅት የሚደርስ ተገቢ ያልሆነ አያያዝ፣ የተቃውሞ ሰልፎች ላይ የጸጥታ ኃይሎች የሚወስዱት ተመጣጣኝ ያልሆነ የኃይል እርምጃ፣ በጋዜጠኞች፣ በሚዲያ፣ በተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎችና ተቃዋሚ ድምጾች ላይ ያነጣጠረ ጥቃትና የቅድመ ክስ እስር፣ ከቦታ ወደ ቦታ የመንቀሳቀስ መብት ላይ የተጣሉ የዘፈቀደ ገደቦች፣ በድርቅ፣ ሕጋዊ ሂደትን ያልተከተለ የቤቶች ፈረሳ እና በግዳጅ ማስነሳት አሳሳቢ ጉዳዮች ሆነው ቀጥለዋል” ሲሉ ማብራራታቸውን ከኮሚሽኑ ድረገጽ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።
ኮሚሰሽኑ ሚያዚያ 26 ባወጣው መግለጫ በክልሉ የተወሰኑ አካባቢዎች በመከላከያ ሰራዊትና ታጣቂዎች መካከል በከባድ መሣሪያ ጭምር ታግዞ እየተካሄደ ባለው የተኩስ ልውውጥ በሲቪል ሰዎች ላይ የሞት፣ የአካልና የንብረት ጉዳት መድረሱን ማስታወቁ ይታወሳል፡፡
ኢሰመኮ በመግለጫው በክልሉ ያሉ የተወሰኑ ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አባላት፣ የክልል ልዩ ኃይሎችን እንደገና የማዋቀር ውሳኔን በመቃወም የተካሄዱ ሰልፎችን መርተዋል/አስተባብረዋል የተባሉ የተወሰኑ ወጣቶች እና ከፋኖ ቡድን ጋር ግንኙነት አላቸው ተብለው የተጠረጠሩ የተወሰኑ ሰዎች እንደታሰሩ አረጋግጫለው ሲል በመግለጫው ማስታወቁን አዲስ ስታንዳርድ መዘገቡ ይታወሳል። አስ