ዜና፡ ኢትዮጵያ እና ግብጽ ተጨማሪ የመሬት መንቀጥቀጥ ያጋጥማቸዋል ሲሉ የዘርፉ ተማራማሪ አስጠነቀቁ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 2/2015 ዓ.ም፡- የካይሮ ዩኒቨርስቲ የጂኦሎጂ ፕሮፌሰር የሆኑት አባስ ሻራኪ ኢትዮጵያ እና ግብጽ በመሬት መንቀጥቀጥ ሊመቱ እንደሚችሉ አስጠነቀቁ። በግብጽ የሚከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ በአስዋን ግድብ አቅራቢያ መሆኑን የጠቆሙት ፕሮፌሰሩ በኢትዮጵያ ደግሞ በህዳሴው ግድብ አቅራቢያ እንደሚሆን ገልጸዋል። በኢትዮጵያ ከህዳሴ ግድብ ሰሜን ምስራቅ 100 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ሚያዚያ 30 ቀን 2015 ዓ.ም በሬክተር ስኬል መለኪያ 4 ነጥብ 4 መጠን ያለው የመሬት መንቀጥቀጥ መመዝገቡን ያስታወቁት ፕሮፌሰሩ ባለፉት መቶ አመታት በኢትዮጵያ ካጋጠሙ የመሬት መንቀጥቀጦች ውስጥ የህዳሴው ግድብ ለተገነባበት አከባቢ የመጀመሪያው እጅግ የቀረበው መሆኑን አመላክተዋል።

የደረሰው መሬት መንቀጥቀጥ በህዳሴ ግድቡ ላይ የሚኖረው ተጽእኖ ይህ ነው የሚባል አይደለም ያሉት ፕሮፌሰር አባስ ሻራኪ በቀጣይ የግድቡ ውሃ 74 ቢሊየን ኪዩቢክ ሜትር ሲደርስ እና የበረታ የመሬት መንቀጥቀጥ ሲስተናገድ ተጽእኖው አደገኛ ይሆናል ብለዋል።

ፕሮፌሰሩ በተጨማሪም ኢትዮጵያን ለሁለት የከፈላት የአፍሪካ ትልቁ ስምጥ ሸለቆ በከፍተኛ ደረጃ የመሬት መንቀጥቀጥ እና የእሳተ ጎመራ የሚያሰጋው ቦታ መሆኑን አስታውቀዋል።

በግብጽ በአሰዋን ሃይ ግድብ 360 ኪሎሜትር እርቀት ላይ በሬከተር ስኬል መለኪያ 4 ነጥብ 2 የሚመጥን የመሬት መንቀጥቀጥ መከሰቱን ያስታወቁት ፕሮፌሰሩ በግብጽ የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ በኢትዮጵያ ከተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ ከአስራ አምስት ደቂቃ በኋላ መሆኑን ጠቁመዋል።

በሁለቱም መሬት መንቀጥቀጦች ምንም አይነት ግንኙነት እንደሌለው ያስታወቁት አባስ ሻራኪ በደቡባዊ ግብጽ የመሬት መንቀጥቀጡ የተከሰተበት አከባቢ ብዙም የመሬት መንቀጥቀጥ ስጋት የሌለበት የተረጋጋ ቦታ መሆኑን ጠቁመዋል። ኢትዮጵያ ታላቁ የስምጥ ሸለቆ የሚገኝባት ቦታ በመሆኗ የመሬት መንቀጥቀጥ እና እሳተ ጎመራ በተደጋጋሚ እንደሚያጠቃት ፕሮፌሰሩ መናገራቸውን ዘገባው አካቷል። አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.