አርሶ አደሮች በባህር ዳር የተቃውሞ ሰልፍ እያደረጉ፤ ፎቶ-ከዶቸ ቨለ ቪዶዮ የተወሰደ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 24/ 2015 ዓ.ም፡- በአማራ ክልል የአፈር ማዳበሪያ እጥረት ሳቢያ በክልሉ የሚገኙ በርካታ አርሶ አደሮች ተቃውሞ ሰለፍ በማድረግ ቁጣቸውን እያሰሙ ይገኛሉ፡፡ ትላንት ግንቦት 23 ቀን በባህር ዳር ከተማ በርካታ ገበሬዎች በከተማ ውስጥ ተቃውሞ ሲያደርጉ ውለዋል፡፡
ከዛሬ ነገ የአፈር ማዳበሪያ ይደርሰኛል በማለት በተስፋ ሲጠባበቅ የቆየው የአማራ ክልል ገበሬ ትዕግስቱ ተሟጦ፣ የክረምት የእርሻ ዝግጅቱን ጥሎ ማዳበሪያ ፍለጋ “ማዳበሪያ ይሰጠን! የማዳበሪያ ችግር ይፈታ!” እያለ ትላንት እና ከትላንት በስቲያ የተቋሞ ሰልፍ አድርጓል፡፡
አዲስ ስታንድርድ በዚህ ጉዳይ ላይ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የህዝብ ግንኙት ኃላፊ አቶ አምሳሉ ጎባውን በስልክ ለማንጋገር ባደረገው ሙከራ “የማደበሪያ ስርጭት ላይ ችግር ነበር፤ ቢሮው ችግሩን ለመቅረፍ ርብርብ እያደረደ ነው፤ ከዚህ በላይ የምለው ነገር የለም” ብለው ተጨማሪ መረጃ ለመስጠት ፍቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል፡፡
የክልሉ ግብርና ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ሓላፊው ሰሞኑን ለአሜሪካ ድምፅ ራዲዮ እንደሚገልጹት፥ የክልሉ መንግሥት፣ 5.2 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለመግዛት፣ ለግብርና ሚኒስቴር ጥያቄ ቢያቀርብም፣ እስከ አሁን የተላከው ግን፣ 1.7 ሚሊዮን ኩንታል ብቻ ነው፡፡ ቀሪው 3.5 ሚሊዮን ኩንታል በፍጥነት እንዲላክለት፣ ቢሮው፣ ከሚመለከታቸው አካላት ጋራ በመነጋገር ላይ ነው፡፡
ኃላፊው አቶ አምሳሉ ጎባው ለዶይቼ ቬሌ በሰጡት ቃል ደግሞ በክልል ደረጃ 9.2 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ለመግዛት ታቅዶ እስካሁን የ5.2 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ በፌደራል ደራጃ ለአማራ ክልል መገዛቱን ጠቅሰው ነገር ግን በተለያዩ ምክንያቶች እስካሁን ለአርሶ አደሩ የደረሰው 700ሺህ ኩንታል ማዳበሪያ ነው ብለዋል፡፡
ከ3.5 ሚሊዮን ኪንታል በላይ የማዳበሪያ እጥረት ያጋጠመው ክልሉ፣ በምዕራብ ጎጃም ዞን የይልማና ዴንሳ ወረዳ የደብረማዊ ቀበሌ አካባቢ አርሶ አደረች እና ከሌሎች ወረዳዎች በተወጣጡ በገበሬዎች ተቃውሞ ቀርቦባቸዋል፡፡
የአማራ ክልል ምክር ቤት የግብርና፣ አካባቢ ጥበቃና ውሀ ሀብት ልማት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ኑርልኝ ብርሀኑ የማዳበሪያ አቅርቦት ችግሩ የተፈጠረው በወቅቱ ማቅረብ ባለመቻሉ፣ የመጣውም ቢሆን በወቅቱ ለአርሶ አደሩ ባለመከፋፈሉና አልፎ አልፎ ማዳበሪያው ለማይመለከታቸው ሰዎች ስለሚደርስ ነው ብለዋል፡፡ በመሆኑም የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት አፋጣኝ እርምት በመውሰድ ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ በአፋጣኝ እንዲደርስ ማድረግ እንደሚኖርባቸው አሳስበዋል፡፡
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኅላፊ ኃይለ ማርያም ከፍያለው (ዶ.ር) ከ2 ነጥብ 3 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ክልሉ ውስጥ መኖሩንና አሁን ድረስ ለአርሶ አደሩ የተሰራጨው 41 በመቶ ብቻ መሆኑን ጠቅሰው ችግሩ ያለውም ከዚህ ላይ እንደኾነ ያነሳሉ፡፡
ክልሉ ውስጥ ከከረመው እና በአዲስ ከገባው የአፈር ማዳበሪያ ውስጥ 96 በመቶ የሚኾነው የአፈር ማዳበሪያ ከዩኔኖች ወደ መሠረታዊ የሕብረት ሥራ ማኀበራት እንጂ ወደ አርሶ አደሮች ባለመሰራጨቱ ክፍተት መፈጠሩን ገልፀዋል፡፡ ይህም የሆነው የፌደራል መንግሥት ለክልሉ ግዥ ከፈጸመው የአፈር ማዳበሪያ ውስጥ መጋቢት እና ሚያዚያ ላይ ሙሉ በሙሉ የአፈር ማዳበሪያ ወደ ክልሉ ባለመግባቱና በዚህ ምክንያት 50 በመቶ የሚሆነው የአፈር ማዳበሪያ ወደ ክልሉ ባለመግባቱ ነው ብለዋል፡፡
በተጨማሪም በክልሉ ውስጥ ከከረመው እና በአዲስ ከገባው የአፈር ማዳበሪያ ውስጥ 96 በመቶው ወደ መሠረታዊ የኀብረት ሥራ ማኀበራት ተሰራጭቶ እያለ ለምን ወደ አርሶ አደሮች ያለመድረሱ ክፍተት የወረዳዎች መኾኑን መውሰድ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ ከዞን እስከ ቀበሌ የግብዓት ስርጭት ኮሚቴ ተቋቁሟል የሚሉት ዶክተር ኃይለማርያም በእጃችን ያለው የአፈር ማዳበሪያ ለምን አልደረሰም የሚለውን መመለስ ያለበትም ኮሚቴው መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በሀገር ደረጃ ተፈጥሮ በነበረው የውጭ ምንዛሬ እጥረት ምክንያት የፌደራል መንግስት ለክልሉ ማቅረብ የነበረበትን የአፈር ማዳበሪያ ሙሉ በሙሉ አለማድረሱ ክፍተት መኾኑን የጠቀሱት ኃላፊው ክፍተቱን ለመሙላት ጥረት እያደረገ ነው ብለዋል፡፡ ነገር ግን መቅረብ የሚገባው ማዳበሪያ አልቀረበም ብሎ ለመጠየቅም በእጃችን ያለውን ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች ሙሉ በሙሉ ማሰራጨት ነበረብን ሲሉ ለአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ተናግረዋል፡፡
ከሰሞኑ ቅሬታ በተነሳባቸው ምሥራቅ ጎጃም፣ ምዕራብ ጎጃም እና አዊ አካባቢዎች የሚዘራው በቆሎ ነው የሚሉት ኅላፊው ለበቆሎ ዘር የሚበቃ የአፈር ማዳበሪያ አለ ሲሉ ገልፀው ቀጣይ ጤፍ፣ ስንዴ እና ሌሎች አዝርዕቶችን ለሚዘሩ አርሶ አደሮች ደግሞ ከመጪው ሰኞ ጀምሮ የሚጓጓዝ ስለሚኾን ተደራሽ ማድረግ ይቻላል ብለዋል፡፡
አሁን ላለው የእርሻ ሥራ በቂ የአፈር ማዳበሪያ አለ፤ እሱን ለአርሶ አደሮች አሰራጭቶ ቀሪውን መጠየቅ ምክንያታዊነት ነው ነገር ግን አሁን ያለው የአፈር ማዳበሪያ ለሁሉም አርሶ አደሮች እና አዝርዕት አይደርስም ብሎ ማስቀመጥ ተገቢ አይደለም ብለዋል፡፡ አክለውም በየደረጃው ያሉ የግብዓት ኮሚቴዎች መጋዘን ውስጥ ያለውን ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች በፍትሐዊነት ማሰራጨት ይገባል ብለዋል፡፡ አስ