ዜና፡ በአማራ ክልል ምሥራቅ ጎጃም ዞን ደብረ ኤሊያስ ወረዳ በምትገኝ ቤተክርስቲያን ቅጥር ግቢ ውስጥ በተከፈተ ጥቃት በርካታ ሰዎች መሞታቸው ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 24/ 2015 ዓ.ም፡- በአማራ ክልል ምሥራቅ ጎጃም ዞን ደብረ ኤሊያስ ወረዳ በምትገኝ ቤተክርስቲያን ቅጥር ግቢ ውስጥ የመንግስት የመንግስት ፀጥታ ሀይል በተከፈተ ጥቃት በርካታ ሰዎች መሞታቸው ተገለፀ፡፡ የደብረ ኤልያስ ወረዳ ሰላምና ፀጥታ ፅ/ቤት፤ በደጎልማ ቀበሌ የሚገኘው የስላሴ አንድነት ገዳም ውስጥ ሀይማኖትን ሽፋን በማድረግ እና በገዳሙ ተሸሽገው በገዳሙ ውስጥ ወታደራዊ ስልጠና እየጡ ምሽግ በመስራት መሳሪያ በመግዛት እንዲሁም ከመንግስት ያፈነገጡ ሰዎችን አሰባስበዋል ያለቸው አካላት ላይ መከላከያ እርምጃ መውሰዱን አስታውቋል

ገዳሙ የሀይማኖት አባቶችን ፣ታዋቂ የሀገር ሽማግሌዎችን የመንግስት አመራሮችን እየገደሉ በህግ ላለመጠየቅ የሚጥሩ የታጠቁ ሰዎች የሚኖሩበት ገዳም ሆኗል ያለው ጽ/ቤቱ መከላከያ የወሰደው እርምጃ በእምነት ተቋሙ ላይ ምንም አይነት ውድመት አላደረሰም ብሏል፡፡

የወረዳ ሰላምና ፀጥታ ጽ/ቤት ይህን ይበል እንጂ ግጭት በከባድ የጦር መሣሪያዎች ጭምር የተከናወነ በመሆኑ “ቤተክርስቲኑ ላይ ጉዳት ድርሶባታል” ሲሉ የዓይን እማኞች ለዶቸ ቨለ ተናግረዋል፡፡ ምክኒያቱ በግልፅ ባልታወቀ በምዕመኑ እና በመንግስት ፀጥታ ሀይሎች መካከል በተነሳው ግጭት በቤተክርስቲያን ቅጥር ግቢ የነበሩ በርካታ ምዕመናን በከባድ መሳሪያ በታገዘ ጥቃት ህይወታቸው ማለፉንና ሌሎቹ መበተናቸውን ዶቸ ቨለ  የዓይን እማኞች ዋቢ በማድረግ ዘግቧል

በገዳሙ ከ600 በላይ ሰዎች ይኖሩ እንደነበረ የተናገሩት አንድ አስተያየት ሰጪ ከ95 ከመቶ በላይ ቆስለዋል፣ ተገድለዋል አሊያም ተበትነዋል ብለዋል፡፡ ከ200 በላይ የመንግሥት የፀጥታ አካላት ቆስለው በሆስፒታሉ መታከማቸውን የዜና ምንጩ በዘገባው አካቷል፡፡ ግጭቱ ለተከታታይ አምስት ቀናት ከተካሄደ በኋላ ከትልንት በስቲያ እኩለ ቀን አካባቢ መቆሙን እማኞቹ ተናግረዋል።

የደብረ ኤልያስ ወረዳ ሰላምና ፀጥታ ፅ/ቤት የግጭቱን ምንስዔ ግልፅ ባያደርግም የገዳሙን አባቶችም ትክክል አይደላችሁም የወንጀለኛ መደበቂያ መሆን ለገዳሙም ጥሩ አይደለም በማለት በሀይማኖት አባቶች ፣በሀገር ሽማግሌዎች ፣ በመንግሥት ከፍተኛ አመራሮች እና በዞን ሀገረ ስብከት የሀይማኖት አባቶች ተጠይቀው ከማስተካከል ይልቅ ተግባሩን በመቀጠላቸው መንግስት እርምጃ መውሰዱን በመግለጫው አመላክቷል፡፡

አንዳንድ ሚዲያዎች ወረዳውን ለማጠልሸት እና ህዝብን ከመንግሥት ለማጋጨት ከሚያሰራቹት የሀሰት አሉባልታዎች ህብረተሰቡ ሳይረበሽ ከፀጥታ ሀይሉ ጎን በመቆም አካባቢውን ተደራጅቶ እንዲጠብቅ አሳስቧል፡፡

እናት ፓርቲ ትላንት ባወጣው መግለጫ ጎጃም ደብረ ኤልያስ በሚገኘዉ የቅድስት ሥላሴ ገዳም አካባቢ በከባድ መሣሪያ የተደግሮ እየተካሄደ ባለው ጥቃት በገዳሙ የሚገኙ መናንያን እንደተገደሉ መሆኑን መረጃ ደርሶኛል ሲል ገልጿል፡፡ በተመሳሳይ በአርሲ ሀገረ ስብከት በጢዮ ወረዳ በጨፌ ሚሶማ ቀበሌ ገበሬ ማኀበር ከአሰላ ከተማ በቅርብ ርቀት በሚገኘው በዴራ አማኑኤል አጥቢያ ቤተክርስቲያን ላይ ካህናትና ምዕመናን፤ በታጣቂዎች በተሰነዘረ ጥቃት ዘግናኝ ጭፍጨፋና ግድያ ተፈጽሞባቸዋል ብሏል።

ድርጅቱ መንግሥት በደብረ ኤሊያስ በቅድስት ሥላሴ ገዳም አካባቢ የጀመረውን በከባድ መሣሪያ የታገዘ መጠነ ሰፊ ጥቃት በአስቸኳይ በማቆም ለተፈጸመው ግድያና ለወደሙ ነዋያተ ቅድሳት ተጠያቂነት እንዲኖር፤ ስለጥቃቱ ሁኔታ ለእምነቱ ተከታዮች ማብራሪያ እንዲሰጥ እንዲሁም የተስተዋሉ ችግሮች ካሉም በሰላማዊ መንገድ ብቻ እንዲፈቱ ጠይቋል።

የኦርቶዶክስ ሃይማኖት አባቶችና ምዕመናን በታጣቂ ቡድን ዘግናኝ ጭፍጨፋ ሲደረግባቸው ይህ የመጀመሪያ አይደለም ያለው ፓርቲው እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በወለጋ ምድር የተከናወነው ጅምላ ጭፍጨፋ የዚሁ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት አንድ ማሳያ ነው ብሏል። በዚህም መንግስት ለህዝብ ያለውን ንቀት በተደጋጋሚ አሳይቷል ሲል ከሷል።አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.