አዲስ አበባ፣ ሓምሌ 1/2015 ዓ.ም፡– ለ30 ዓመታት የአማራና የትግራይ ክልሎች የይገባኛል ጥያቄ የሚያነሱባቸው አካባቢዎች ጉዳይ በህዝበ ውሳኔ እንዲፈታና ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የአማራ ክልል መንግስት ጥረት እያደረገ መሆኑን የክልሉ የኮሙዩኒኬስን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ትላንት በሰጡት መግለጫ አስታወቁ፡፡
የማንነትና የወሰን ጥያቄ ቢያንስ ከ30 አመታት በኋላ በህዝበ ውሳኔ እንዲፈጣ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን የገለፁት ኃላፊው ሕገ መንግስት ለማሻሻል ጥረቶች መጀመራቸውን አስታውሰው ጥያቄ ማቅረብ መቀጠላቸውንና በጥሩ ሁኔታ እየሄዱ መሆኑን አመላክተዋል፡፡ ጥያቄዎቻቸው እንዲመለሱም ዝግጁነት ስለሚያስፈልግ ክልሉን ሰላም ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አክለው ገልፀዋል፡፡
ክልሉ የሰሜኑ ጦርነት ካደረሰው ጫና ገና ያልተላቀቀ መሆንን የገለፁት ኃላፊው በአንዳንድ አካባቢዎች አሁንም የሰላም እጦትና፣ ሕገወጥ ድርጊቶች እንዳሉ ገልፀዋል፡፡ አቶ ግዛቸው በነፃነት በመዘዋወር በተመለከተ በአንዳንድ አካባቢ ችግር መኖሩን ጠቅሰው የመንገድ መዘጋት፣ የመታገት አደጋዎች፣ ግድያ፣ ውድመትና ዘረፋ የክልሉን ሰላም በመደፍረስ አሉታዊ ተጽዕኖ እያደረሱ ነው ብለዋል፡፡
ክልሉ፣ የሰላም እጦት እየተፈታተኑት ነው ያሉት አቶ ግዛቸው ለዚህ ደግሞ ውስጣዊ እና ውጭያዊ ጫናዎችን እንደ ምክንያትነት አቅርበዋል፡፡ በእነዚህ ችግሮችም የተነሳም አሁንም ድረስ በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ የሰው ህይወት ባለተገባ መንገድ የሚጠፋበት፣ ንብረት የሚወድምበት፣ አካል የሚጎድልበት ሁኔታ እየተስተዋለ ነው ብለዋል፡፡
ማህበረሰቡ በነፃነት ለመንቀሳቀስ የሚሰጋበትና የስነ-ልቦና ጫና ውስጥ እንዲገባ የሚያደርጉ ሁናቴዎች በአንዳንድ አካባቢዎች አለመቀረፋቸውን አመላክተዋል፡፡
የሰላምና የልማት ጥያቄዎች ለአመታት እየተንከባለሉ “ለአሁኑ ትውልድ እዳ እየሆኑ የመጡ የማንንት ጥያቄዎች አሉ” በማለት በመግለጫቸው የገለፁት ኃላፊው “የሕገ መንግስት መሻሻል ጥያቄዎች፣ የዜጎች መብት መከበር ጥያቄዎች፣ የተዛባውን ትርክት የማረም ጥያቄዎች፣ ከድህነት የመውጣት ጥያቄዎች፣ አጠቃላይ የአማራ ህዝብ ጥያቄዎችና ዘላቂ ጥቅሞች የሚረጋገጡት እንዲሁም የተዛባው ትርክት የሚስተካከለው፣ የወሰን፣ የማንነት ጥያቄዎች የሚስተካከለው ውስጠ አንድነትችንን አጠናክረን በወንድማማችነትና በእህትማማችነት በኢትዮጵያ ጥላ ስር ብስለት ያለው ብልሃት የተሞላበት የሃሳብ ትግል መድረግ ስንችል ነው” ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚንስትር አብይ ሰኔ 29 ፣ 2015 ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ ለ 30 ዓመት በትግራይ እና በአማራ ክልል መካከል የይገባኛል ጥያቄ የሚነሱባቸውን አካባባዎች ውዝግብ ለመፍታት ሁለቱ ህዝቦች በሰከነ መንገድ እንዲመክሩበት መክረዋል፡፡ በመሬት ምክንያት መባላት መገዳደል አያስፈልግም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰከነ መንገድ በመነጋገር ከመፍታት ውጭ ያለው መንገድ ጥሩ አይደለም ሲል አሳስበዋል፡፡አስ