ዜና፡ በትግራይ ጉብኝት እያካሄዱ የሚገኙት አቡነ ማትያስ ከክልሉ ጊዜያዊ ፕሬዝዳንት ጋር ተገናኙ፤ ግዜያዊ አስተዳደሩ በቤተክርስቲያኗ ጉዳይ ጣልቃ እንደማይገባ አቶ ጌታቸው ገልጸዋል

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 3/2015 ዓ.ም፡- በትግራይ ጉብኝት እያካሄዱ የሚገኙት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ከክልሉ ጊዜያዊ ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ጋር ተገናኝተው መወያየታቸው ተገለጸ። ግዜያዊ አስተዳደሩ በቤተክርስቲያኗ ጉዳይ ጣልቃ እንደማይገባ አቶ ጌታቸው ረዳ እንደገለጹላቸው ከትግራይ ቴሌቪዥን ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።

ከውይይቱ በኋላ ልዑካኑን የመሩት አቡነ ማትያስ እና የክልሉ ግዜያዊ ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው መግለጫ ሰጥተዋል። ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በመድረኩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት በትግራይ ክልል የሚገኙ አባቶች በምን ምክንያት በውይይቱ እንዳልተገኙ የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ገልጸው የሆነ ሁኖ ግን መወያየት ጥሩ ነበረ፤ በመወያየት ሀሳብን መግለጽ ይቻላል፣ የደረሰውን ችግር መግለጹ ማስረዳቱ አንድ ቁምነገር ነው፤ ይሁንም አይሁንም ለማለት ውይይት ጥሩ ነበረ፤ የሆነ ሁኖ ከብጹአን አባቶች ጋር አልተገናኘንም ሲሉ ተደምጠዋል። ለወደፊቱ ለመገናኘት ተስፋ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።

በትግራይ ከሚገኙ የቤተክርስቲያን አባቶች ጋር መወያየታቸውን በመድረኩ ላይ ያስታወቁት አቶ ጌታቸው እነሱን የማስገደድ ሃላፊነትም ስለጣንም ፍላጎቱም የለኝም ሲሉ ገልጸዋል። ልዩነቱ ወደ ለየለት ግጭት እንዳያመራ ተቀራርቦ መስራት እንዳለባቸው አምናለሁ ያሉት አቶ ጌታቸው የትግራይ የቤተክርስቲያኗ አባቶች ጥያቄ የነሱ ብቻ ሳይሆን የሁሉም የትግራይ ተወላጅ በተለይ የእምነቱ ተከታዮች ጥያቄ መሆኑን አስታውቀዋል።

የተፈጠረውን ቅሬታ በትክክል መገንዘብ፣ በትክክል ተረድቶ ያንን የሚመጥን ስራ መስራት እንደሚገባ አምናለሁ ያሉት ፕሬዝዳንቱ አቶ ጌታቸው ረፍዶ ይሆናል፣ ዘግይቶ ይሆናል፣ ነገር ግን ሙሉ ለሙሉ ዝግ ነው ብየ አልወስድም ሲሉ ተደምጠዋል።

አንዳንድ የቤተክርስቲያኗ አባቶች በጣም ያልተገባ፣ ከቤተክርስቲያኗ እምነት የራቀ መልዕክት ሲያስተላልፉ ለማስቆም የሞከረ አለመኖሩን የጠቆሙት አቶ ጌታቸው እንደ ብጹዕ አባት በግላችሁ እንኳ አልሞከራችሁም ሲሉ ወቀሳቸውን አቅርበው ይህ ጥያቄ በተደጋጋሚ ከክልሉ ቤተክህነት አባቶች ጋር ባደረጉት ውይይት የሚነሳ ጥያቄ መሆኑን እና ምላሽ ለመስጠት እንደከበዳቸው አመላክተዋል።

በክልሉ በጦርነቱ ምክንያት ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች እገዛ የሚውል 20 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ለጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝደንት አቶ ጌታቸው ረዳ በፕላኔት ሆቴል በተደረገ መርሀግብር ላይ አቡነ ማትያስ እና ልዑካቸው አስረክበዋል።

በመቀሌ ከተማ ጉብኝት ያካሄደው በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፣ የተመራው የሰላም ልዑክ 18 አባላት የያዘ መሆኑን መረጃው አመላክቷል። አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.