አዲስ አበባ፣ የካቲት 16/ 2015 ዓ.ም፡– የንግድና የሰዎች እንቅስቃሴ ገደብ ባለመነሳቱ በአፋር የሚገኙ ተፈናቃዮች እና ተመላሾች በዘላቂነት እንዲቋቋሙ የሚያስችል ሁኔታዎች እንዳይፈጠር ተግዳሮት መሆኑን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
ኮሚሽኑ ይህንን ያስታወቀው የካቲት 15 ቀን 2015 በድረገጹ ይፋ ባደረገው ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሆን በአፋር ክልል የተላዩ ቦታዎች በመገኘት የመስክ ክትትል ማከናወኑን በመግለጫው አመላክቷል።
በተጨማሪም የጦርነት ቀጠና የነበሩ እንደ ጉሊና ወረዳ ፎኪሳ ቀበሌ ባሉ አካባቢዎች ፈንጂ እና መሰል የጦር መሣሪያዎችን በማምከን አካባቢውን ከአደገኛ የጦር መሳሪያዎች የማጽዳት ሥራ በአግባቡ ባለመከናወኑ በተመላሾች ላይ የደኅንነት ሥጋት መፍጠሩን ኢሰመኮ ጠቁሟል፡፡
ክትትል በተደረገባቸው አካባቢዎች ተመላሾች በራሳቸው ሙሉ ፈቃድ የተመለሱ ቢሆንም፤ መደበኛ ኑሯቸውን ለመቀጠል የሚያስችላቸውን ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ለተፈናቃዮች ዘላቂ መፍትሔ ማፈላለግን በተመለከተ ክፍተቶች እንዳሉ የኮሚሽኑ ክትትል ያመላክታል ብሏል፡፡
ከሰሜኑ ጦርነት ጋር በተያያዘ ከሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በአፋር ክልል ዞን ሁለት እና ዞን አራት በኩል በየብስ ትራንስፖርት ወደ ትግራይ ክልል ተጓጉዘው ይገቡ የነበሩ ነዳጅን ጨምሮ የተለያዩ መሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች እንዳይገቡ የተጣለው እገዳ ባለመነሳቱ በሁለቱ ዞኖች ውስጥ የሚደረገውን የንግድ እንቅስቃሴ ከመገደቡ በተጨማሪ በፍጆታ ዕቃዎች ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ማስከተሉንም አስታውቋ።
በአከባቢው ነዋሪዎች ላይ ጦርነቱ ካስከተለባቸው የሰብአዊ ቀውስ እና ወቅቱን የጠበቀ የሰብአዊ ድጋፍ ካለመቅረቡ በተጨማሪ የንግድ እንቅስቃሴው ገደብ ባለመነሳቱ ምክንያት እየደረሰባቸው ያለው ያልተገባ ኢኮኖሚያዊ ጫና፤ ተፈናቃዮች እና ተመላሾች በዘላቂነት እንዲቋቋሙ አስቻይ ሁኔታዎች እንዳይፈጠር ተግዳሮት መሆኑን መግለጫው አመላክቷል። ኮሚሽኑ በትግራይ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች የሚኖሩ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ዳግም ግጭት ሊከሰት ይችላል የሚል ሥጋት እንዳለባቸው መግለጻቸውን አስታውቋል።
መንግሥት በአፋር ክልል በዞን ሁለት፣ በዞን አራት እንዲሁም በሰመራ ከተማ ለሚገኙ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች እና ተመላሾች በቂ፣ ወቅቱን የጠበቀ እና ተደራሽ የሆነ የሰብአዊ ድጋፍ የማቅረብ ኃላፊነቱን በተገቢው መንገድ መወጣት አለበት ሲል አሳስቧል።
የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችና ተመላሾች በቂ፣ ወቅቱን የጠበቀ እና ተደራሽ የሆነ ምግብ፣ ውሃ፣ መጠለያ፣ የጤና ፣ ትምህርት እና ሌሎች ማኅበራዊ አገልግሎቶችን ያካተተ የሰብአዊ ድጋፍ እየቀረበላቸው እንዳልሆነ ባከናወነው ክትትል መመልከቱን አስታውቋል፡፡ በተለይ በጦርነቱ ወቅት የሕክምና ቁሳቁሶች፣ የመድኃኒቶች እና የክትባት ማስቀመጫ ፍሪጅን ጨምሮ በርካታ የጤና አገልግሎት ተቋማት በመዘረፋቸውና በመውደማቸው የሕክምና ቁሳቁስ እና መድኃኒት እጥረት መፈጠሩን ገልጿል።
“በክልሉ የሚገኙ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች የሰሜኑ ጦርነት ካስከተለባቸው የሰብአዊ ቀውስ በአግባቡ ለማገገም እና እራሳቸውን ችለው ለመኖር በሚያደርጉት ጥረት የንግድ እንቅስቃሴ ገደቡ አለመነሳቱ ተጨማሪ የኢኮኖሚ ጫና እየፈጠረባቸው እና መደበኛ ኑሯቸውን እንዳይቀጥሉ ከማድረጉ ባሻገር በዘላቂነት እንዳይቋቋሙ እንቅፋት ሆኗል” ሲሉ የኢሰመኮ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ መናገራቸው በመግለጫው ተካቷል።አስ