በብሩክ አለሙ @Birukalemu21 እና
መድኃኔ እቁባሚካኤል @Medihane
ያቤሎ፣ ቦረና፣ መጋቢት 4/ 2015 ዓ.ም፡– በደቡብ ኦሮምያ በድርቅ ክፉኛ የተጎዳው ቦረና ዞን ዋና ከተማ ያቤሎ የሚገኙ ነዋሪዎች ድርቁ የሚያደርስባቸው ጫና ሳያንስ በእነሱ ስም የመጣ እርዳታ ሙስና እየተሰራበት ይገኛል። የእርዳታ እህሉን እንዲያከፋፍሉ ስልጣን የተሰጣቸው ሃላፊዎች ለእርዳታ ከመጣው እህል ውስጥ በመቀነስ ለግል ጥቅማቸው እያዋሉት እንደሚገኝ ተጠቁሟል።
ጉዳዩ ያሳዘናቸው የማህበረሰቡ አባላት በአከባቢው ለተገኘው የአዲስ ስታንዳርድ ጋዜጠኞች ቡድን ያሰረሱት መረጃ እንደሚያመለክተው የክልሉ የእርዳታ እና ስጋት ተቋም መለያ ‘’ቡሳ ጎኖፋ’’ ያለበት እና ለእርዳታ አቅርቦት ብቻ መሆኑን የሚገልጽ ፅሁፍ የያዘ የዱቄት ምርት ለገበያ በመቅረብ ላይ ይገኛል። በያቤሎ ከተማ አቅራቢያ የዱቄት ምርቱ በመሸጥ ላይ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የእርዳ እህል ወደ አከባቢው ይዘው የሚመጡ ሰዎች እርዳታው ተፈናቃዮች ወዳአሉበት ቦታ በመውስድ እራሳቸው ማከፋፈል አለባቸው፤ የእርዳታ እህሉን በአከባቢው በሚገኙ ማካማቻዎች ማስቀመጥ የለባቸውም ሲል በያቤሎ ከአጋሮቹ ጋር በመሆን እርዳታ ለማቅብ የተገኘው ታዋቂው የኦሮምኛ አርቲስት ሺመልስ አባቡ ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጿል። ከተለያዩ በጎ አድራጊ ግለሰቦች የሚሰበሰበው እርዳታ በድርቁ ለተጎዱ ሰዎች በቀጥታ እየደረሰ አለመሆኑን ተረድተናል ሲል አርቲስቱ አሳስቧል። በከተማዋ የሚገኙ የአከባቢው ባለስልጣናት እና እራሳቸውን የእርዳታ አቅርቦት አስተባባሪነን ብለው የሰየሙ ሰዎች ወደ ዞኑ የሚመጡ የእርዳታ እህሎች በመጋዘኖቻቸው እንዲከማቹ እንደሚፈልጉ ተረድተናል ያለው ሺመልስ እኛም ይዘን የመጣነውን የእርዳታ እህል በመጋዘኖቻቸው እንድናራግፍ ነግረውን ነበር ሲል ገልጿል። እኛ ወደእዚህ የመጣነው የተጎዳውን ህዝባችንን እርዳታ ይዘን ለመድረስ ነው እንጂ እርዳታውን ጣል አድርገን ለመመለስ አይደለም ሲል የነገረን አርቲስት ሺመልስ ባለስልጣናቱ ወደ አዘጋጁት መጋዘን እንዲያራግፉ ጫና እንደተደረገባቸው አስታውቋል።
ከዚህ በተጨማሪም በመጠለያ ጣቢያዎች የማይገኙ የአከባቢው የድርቅ ተጠቂዎች በቂ እርዳታ እየተሰጣኘው አለመሆኑን ተነግሮናል ያለው አርቲስቱ ባለስልጣናቱ ባዘጋጇቸው ማከማቻዎች ማስቀመጡ ተጎጂዎች ባግባቡ እንዳይደርሳቸው አድርጓል ሲል ተችቷል። ማንኛውም የቦረናን የድርቅ ተጠቂዎች መርዳት የሚፈልግ ተጠቂዎቹ ወደ ሚገኙበት በቀጥታ በመሄድ እርዳታውን እንዲያደርስ መልዕክቱን አስቀምጧል።
በተመሳሳይ በውጭ ሀገራት የሚገኙ የዲያስፖራ አባላትን የተሰባሰበ እርዳታ ለማድረስ ወደ ያቤሎ የመጣ ግለሰብ በበኩሉ እርዳታውን በወረዳው በሚገኝ ማከማቻ እንዲያራግፉ ጫና እንደተደረገባቸው ለአዲስ ስታንዳርድ አስታውቋል።
በያቤሎ ከተማ የሚኖሩ እና ለደህንነታቸው ሲሉ ስማቸው እንዲጠቀሱ ያልፈለጉ ሰዎች ለአዲስ ስታንዳርድ እንዳስታወቁት ወደ ከተማው ከሚገባው የእርዳታ እህል እጅግ ያነሰው ለተጎጂዎች እየተከፋፈለ ይገኛል።
ቸርቻሪዎች ለእርዳታ በሚል የሚመጣን ዱቄት በግልጽ ለመግዛት በመጠየቅ ላይ እንደሚገኙ የጠቆመን አንድ የከተማዋ ነዋሪ በማከማቻ መጋዘኖች የሚገኙ አቅርቦቶቹ በሙሰኞች ባለስልጣናት ተሽጠው ኪሳቸውን ማዳለብ መጨረሻቸው ይሆናል የሚል እምነት እንዳለው አስታውቋል።
በሌላ በኩል በያቤሎ የሚገኙ ነጋዴዎች ለተጎጂው ማህበረሰብ የመጣን እርዳታ ላለመግዛት መግባባት ላይ መድረሳቸውን ለደህንነቱ ሲባል ስሙ ያለተገለጸ የእህል ምርት አከፋፋይ ነጋዴ ነግሮናል።
የቀረቡትን ክሶች ይዘን ምላሽ ለማግኘት የሚመለከታቸውን የአከባቢው ሃላፊዎች አነጋግረናል። የዞኑ የአደጋና ምላሽ ቢሮ አስተባባሪ የሆኑት ሮባ ዳንጌ እንዳስታወቁት ወደ ዞኑ የሚመጡ የእርዳታ እህሎችን በቢሯቸው በኩል ለመረከብ እና ለማከፋፈል የሚያስችል አሰራር መዘትጋቱን ጠቁመዋል። የቀረበባቸውን ክስ አስተባብለው እንዲያውም በተቃራኒው የእርዳታ እህል ለማድረስ የሚመጡ አካላት ትራንስፖርት ተዋውለው የሚመጡት እስከ ያቤሎ ከተማ ድረስ ብቻ በመሆኑ ተጎጂዎች ወዳሉበት ለማድረስ እንገደዳል ሲሉ ገልጸዋል። እንዲህ አይነት ክስ ከማንም ቀርቦብን አያውቅም ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። ለሽያጭ የቀረቡ እህሎች የሚያሳዩ በፎቶ የተደገፉ ማስረጃዎች እንዳሉ የጠቆምናቸው ሃላፊው ፎቶዎቹን ከእርዳታ ማዘኖች በማንሳት እና በማዘዋወር ለክፉ አላማ መጠቀም ቀላልነው ሲሉ አስተባብለዋል።
የያቤሎ ከተማ ከንቲባ ጉዮ ካሊቻ በተመሳሳይ ክሶቹን አጣጥለው የዞኑ አስተዳደር ለእርዳታ የመጣ ምንም አይነት እህል አላከማቸንም ብለዋል። ወደ ከተማ ለእርዳታ የመጡ ሰዎችን መጠለያ ሰጥተን የእርዳታ እህል እያቀረብን እንገኛለን ሲሉ የገለጹልን ከንቲባው ከከተማዋ ውጪ በሚገኙ ወረዳዎች እየተደረገ ስላለው እርዳታ መረጃው የለኝም ብለዋል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ በሳምንቱ መገባደጃ ቀናት የኦሮምያ ክልላዊ መንግስት ባወጣው መግለጫ ከክልሉ መንግስት ፍቃድ ውጭ በግልም ሆነ በቡድን ከቦረና ድርቅ ጋር በተያያዘ እርዳታ ማሰባሰብ በጥብቅ ከልክሏል።