አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 6/2015 ዓ.ም፡– በትግራይ ክልል ሐምሌ 9 ይደረጋል የተባለው የኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ የሕገ ቤተ ክርስቲያንን ያላከበረና የቤተ ክርስቲያንን ማዕከላዊነት የሚጥስ በመሆኑ እንዲቆም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ባወጣው መግለጫ ጠየቀ።
ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ እና የትግራይ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ የጳጳሳቱን ሹመት እንዲያስቆሙ ብሎም ሰላም ለማስፈን የሚደረገውን ጥረት በመደገፍ ችግሮቹ በውይይት እንዲፈቱ መንግሥታዊ እገዛ በማድረግ የውይይት መድረክ እንዲያመቻቹልን ሲል ጠይቋል።
ሹመቱ የቤተ ክርስቲያንን አንድነት የሚጎዳና በጦርነት የተጎዳውን ሀብት ንብረቱ የወደመበትን ገዳማቱና አብያተ ክርስቲያናቱ የተጎዱበትን ሕዝብ የማይጠቅም ተገቢነት የሌለው በመሆኑ እንዲቆም ሲል መወሰኑን መግለጫው አስታውቋል።
ሲኖዶሱ በመግለጫው ካካተታቸው ውሳኔዎች መካከልም ለሰላም የሚደረገው ጥረት ዘላቂ መፍትሔ እስከሚገኝ ድረስ ግንኙነቱ የማይቋረጥ መሆኑን ያስታወቀበት ይገኛል፡፡
በትግራይ ክልል የሚገኙ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት አባቶች በሳምንቱ መጨረሻ እሁድ ሐምሌ 9 ቀን 2015 ዓ.ም በአክሱም ጽዮን የአዳዲስ ጳጳሳት ሹመት እንደሚያካሂዱ መግለጻቸውን መዘገባችን ይታወሳል። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሲኖዶስ እና በትግራይ ክልል በሚገኙ የእምነቱ አባቶች በመንበረ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን መካከል የተፈጠረው ልዩነት ባልተፈታበት ሁኔታ የትግራይ አባቶች ሹመቱን ለማካሄድ መወሰናቸውን ለመገናኛ ብዙሃን በላኩት ደብዳቤ ማሳወቃቸውን በዘገባችን አካተናል። የሚዲያ ሽፋን በጠየቁበት ደብዳቤ እንደተመላከተው በእለቱ የአስር ጳጳሳት ሹመት እንደሚካሄድ ተጠቁሟል።
በሳምንቱ መጀመሪያ ቀናት በትግራይ ጉብኝት ያካሄዱት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በክልሉ ጉብኝት ቢያካሂዱም በክልሉ ከሚገኙ የቤተክርስቲያኗ ብጹአን አባቶች ጋር ተገናኝተው አለመምከራቸው ይታወሳል። አስ