ከሱዳን ተሰደው ወደ ኢትዮጵያ የገቡ ስደተኞች ፎቶ-: UNOCHA
አዲስ አበባ፣ ግንቦት፣ 4/ 2015 ዓ.ም፡- በሱዳን በተከሰተው ጦርነት ምክንያት እስከ ትናንትና ድረስ ከ17 ሺህ 444 በላይ የሚሆኑ የ67 ሀገራት ዜጎች ስደተኞች ወደ ምዕራብ ጎንደር ዞን መግባታቸውን የዞኑ አስተዳደር አስታወቀ፡፡
የምዕራብ ጎንደር ዞን የመንግስት ኮሙኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ ፋንታሁን ቢሆነኝ በተለይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንዳስታወቁት፤ በሱዳን በተቀሰቀሰው ጦርነት ምክንያት ከአውሮፓ፣ አሜሪካ፣ እስያና አፍሪካ እንዲሁም በሌሎች አህጉራት የሚገኙ የ67 ሀገራት ዜጎች በስደት ወደ ኢትዮጵያ ገብተዋል።
የሱዳን ጦርነቱ የተቀሰቀሰውን ግጭት በመሸሽ ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ከመጡ መካከል ኢትዮጵያውያን እንደሚገኙ የገለፁት አስተዳዳሪው ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ስደተኞች ቁጥር አሁንም እየጨመረ መሆኑን ጠቁመው ወደ ምዕራብ ጎንደር ዞን ለገቡ ስደተኞች የተለያዩ ድጋፎች በመንግስትና በማህበረሰቡ እየቀረበ መሆኑን ገልፀዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ትላንት ባወጣው መግለጫ ከ18 ሺህ በላይ ስደተኞች ወደ መተማ ድንደር መግባታቸውን ገልፆ ከሁለት ቀን በፊት ከገቡ 630 ከሚጠጉ ስደተኞች ውስጥ 64 በመቶ የሚሆኑት ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን አስታውቋል፡፡ በተጨማሪም 440 የሚሆኑ ስደተኞች በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ኩርሙክ ድንበርን አቋርጠው ወደ ኢጥዮጵያ ገብተዋል ሲል አክሎ ገልጧል፡፡
አስተዳዳሪው ስደተኞቹ ወደ ኢትዮጵያ በሚገቡበት ጊዜ ችግር እንዳይገጥማቸው ከሰላምና ጸጥታ፣ ከሎጅስቲክስ፣ ከጤና እንዲሁም የተለያዩ የሰብዓዊ ድጋፎች ጋር የተያያዙ ስራዎችን የሚያከናውን ግብረ-ኃይል ተቋቁሞ ወደ ስራ መግባቱን ገልጸዋል። እንደ አቶ ፋንታሁን ገለጻ፤ ከሱዳን የመጡት ዜጎች የጤና እክል በሚገጥማቸው ወቅት መተማ ዮሐንስ ከተማ በሚገኘው የጤና ተቋማት እየታከሙ ይገኛል። ሪፈር ለሚያስፈልጋቸው ህሙማን ደግሞ ወደ ገንዳ ውሃ ሆስፒታል ሄደው አገልግሎት እንዲያገኙ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
ከትራንስፖርት ጋር ተያይዞ ችግር እንዳይከሰትና የተጋነነ የታሪፍ ጭማሪ እንዳይኖር ከ460 በላይ የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ለአገልግሎት እየዋሉ መሆኑን ኃላፊው ጠቅሰው አክለውም ስደተኞቹን ከአደጋ ለመከላከል ካሉት መጠለያ ጣቢያዎች በተጨማሪ አዳዲስ ለመጠለያ የሚሆኑ ቦታዎች ላይ ከዓለም አቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ጋር በጋራ በመሆን ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል።
የሎጂስቲክስ የአቅርቦት ችግር፣ የሰብዓዊ ድጋፍ ሙሉ በሙሉ ከማሟላት አኳያ ችግሮች እንዳሉ የተናገሩት አቶ ፋንታሁን፤ ነገር ግን ችግሩን ለመቅረፍ ማህበረሰቡ፣ ቀይ መስቀል፣ ግብረ-ሰናይ ድርጅቶች እንዲሁም በዞን ደረጃ ካለው የምግብ ዋስትናና አደጋ መከላከል ጋር በጋራ እየሰራን ነው ብለዋል፡፡