ዜና፡ በሶማሌ ክልል በደረሰ የጎርፍ አደጋ 44 ሰዎች መሞታቸው ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 4/2015 ዓ.ም፡- በሶማሌ ክልል እየጣለ ያለው ዝናብ በአስከተለው ጎርፍ፣ የ44 ሰዎች ሕይወት ያለፈ ሲሆን፣ ከ19ሺሕ በላይ እንስሳትም መሞታቸውን የክልሉ አደጋ መከላከል እና ዝግጁነት ቢሮ የአደጋ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ቢሮ አስታውቋል።

በክልሉ ባለፉት ሣምንታት ጀምሮ በ38 ወረዳዎች ውስጥ በጣለው ከባድ ዝናብ የዋቢ ሸበሌ፣ ገናሌ፣ ወይብና ጀረር ወንዞች ከመጠን በላይ ሞልተው በመፍሰሳቸው በወንዞቹ አቅራቢያ የሚገኙ 211 መንደሮች በጎርፍ ተጎድተዋል ተብሏል። የቢሮው የቅድመ ማስጠንቀቂያ ቡድን መሪ በሺር አረብ እንደገለጹት በክልሉ ሸበሌ፣ አፍዴር፣ ኤረር፣ ኖጎብና ጀረር ዞኖች በሚገኙ ዘጠኝ ወረዳዎች የጎርፍ አደጋ አጋጥሟል።

ጎርፉ ባስከተለው አደጋ ሕይወታቸውን ካጡት 44 ሰዎች ውስጥ 15ቱ፣ በጭነት መኪና ተሳፍረው የነበሩና ከእነተሽከርካሪው በወንዙ የተወሰዱ ሲኾኑ፣ ቀሪዎቹ ደግሞ፣ በድንገተኛ ደራሽ ጎርፍ እና በወንዞች ሙላት ተወስደው መሞታቸውን ቪኦኤ ዘግቧል

በመንደሮቹ በደረሰው የጎርፍ አደጋ 30 ሺህ 249 አርብቶ አደሮችና ከፊል አርብቶ አደሮች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውን ከኢዜኣ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

45 ሺህ ሄክታር ያህል መሬት ላይ የነበረ የሰብል ቡቃያ መውደሙንም ለኢዜኣ የገለፁት አቶ በሺር፣ በተጨማሪም 108 የንጹህ መጠጥ ውሃ ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶች፣ ጤና ጣቢያዎችና ኬላዎች ላይ ጉዳት መድረሱን ጠቅሰው፣ 317 የውሃ መሳቢያ ሞተሮች በጎርፍ መወሰዳቸውን ተናግረዋል።

በሀገር መከላከያ ሠራዊት ድጋፍ በሄሊኮፕተርና በጀልባዎች በመታገዝ ተጎጂዎች የጎርፍ ጉዳት ከደረሰባቸው አካባቢዎች ለቀው ደረቃማ ወደ ሆኑ ስፍራዎች እንዲሰባሰቡ መደረጉን አስታውሰዋል፡፡

እስካሁን ለ10 ሺህ 512 ወገኖች ከ3 ሺህ 40 ኩንታል በላይ ሩዝ፣ የዳቦ ዱቄትና አልሚ ምግብ እንዲሁም 438 ሊትር የምግብ ዘይት ቀርቧል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በኢትዮጵያ የሜቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት የሶማሌና አጎራባች ክልሎች ቅርንጫፍ ዳይሬክተር ዘሪሁን ኃይለማርያም እንደገለጹት በአብዛኛው የክልሉና በምስራቁና በደቡብ ምስራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች በአሁኑ ወቅት እየጣለ ያለው ዝናብ በያዝነው ግንቦት ወርም እንደሚቀጥል የሜቲዎሮሎጂ የአየር ትንበያ መረጃዎች ያሳያሉ ብለዋል። ሕዝቡ ከውሃ አካላትና ከወንዞች አካባቢዎች በመራቅ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግም አስጠንቅቀዋል።

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.