ዜና፡ በርካታ ሀገራት ዜጎቻቸውን ከሱዳን ለማስወጣት የኢትዮጵያን መንግስት ትብብር በመጠየቅ ላይ ይገኛሉ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 17/2015 ዓ.ም፡- በሱዳን የተፈጠረው ቀውስ አሁንም አልበረደም። የኢድ አልፈጥር በአልን ተንተርሶ የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት ሙሉ በሙሉ ባይተገበርም የተወሰነ እፎይታ ያገኙ አከባቢዎች መኖራቸውን በርካታ መገናኛ ብዙሃን አመላክተዋል። ይህ የታየው እጅግ ውስን የተኩስ ማቆም ተነሳሽነት ትላንትም ቀጥሎ ሁለቱ ጀነራሎች ለተጨማሪ 72 ሰዓታት ተኩስ ለማቆም መስማማታቸውን የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን አስታውቀዋል። ከኢድ አልፈጥር በአል ጋር በተያያዘ የተደረሰውን የተኩስ አቁም ስምምነት ተንተርሰው በርካታ ሀገራት ዜጎቻቸውን ከሱዳን ለማውጣት ተጠቅመውበታል። ኢኮኖሚክ ታይምስ በድረገጹ እንዳስነበበው በርካታ ሀገራት ዜጎቻቸውን በአፋጣኝ ባለፉት ሶስት ቀናት አስወጥተዋል።

አዲስ በተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነቱን ለመጠቀም እና ዜጎቻቸውን ለማስወጣት ሀገራት ከወዲሁ ጥረት እያደረጉ ይገኛል። በጥረታቸው ውስጥ በተደጋጋሚ እየተነሳ የሚገኘው ደግሞ የኢትዮጵያ ስም ነው። ዜጎቻቸው በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ሱዳን ያቀኑ ሀገራት ለማስወጣት በሚያደርጉት ጥረት የኢትዮጵያ መንግስት ትብብር እየጠየቁ እንደሚገኙ የየሀገራቱ መገናኛ ብዙሃን በመግለጽ ላይ ይገኛሉ።

የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማቭለት ካቩሶልጉ ዜጎቻቸውን ከሱዳን ለማስወጣት እና ወደ ቱርክ እንዲያመሩ ለማድረግ በሚቻልበት ጉዳይ ዙሪያ ከኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር ማውራታቸውን ምንጮቹን ዋቢ በማድረግ አናዶሉ ዘግቧል። በሱዳን የሚገኙ የቱርክ ዜጎች በሶስት ቡድን ተከፍለው እንዲወጡ ለማድረግ የሚያስችል ዝግጅት መከናወኑን ያመላከው የዜና ወኪሉ ከሶስቱ ቡድኖች ውስጥ ሁለቱ ቡድኖች ኢትዮጵያ ድንበር ላይ እንደሚገኙ ጠቁሟል። የቱርኩ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከአቶ ደመቀ ጋር የተነጋገሩትም በኢትዮጵያ በኩል በረራ ተመቻችቶላቸው ወደ እስታንቡል እንዲያመሩ ለማስቻል መሆኑም ተጠቁሟል።

የጋና መገናኛ ብዙሃን በበኩላቸው የሀገራቸው የውጭ ጉዳይ ባለስልጣናT በሱዳን የሚገኙ ጋናውያንን በኢትዮጵያ በኩል ለማስወጣት ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር እየሰራ እንደሚገኝ አስነብበዋል።

የሮማንያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትርም በኢትዮጵያ በሚገኘው ኢምባሲው አማካኝነት ዜጎቹን ለማስወጣት እየጣረ እንደሚገኝ የሀገሪቱ መገናኛ ብዙሃን አስታውቀዋል።

የኬንያ መንግስት አንድ መቶ የሚሆኑ በሱዳን ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የነበሩ ዜጎቹን በኢትዮጵያ በጎንደር በኩል ማስወጣቱን የሀገሪቱ ጋዜጦች ማስነበባቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

በሌላ በኩል በሱዳን ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የነበሩ ናይጀሪያውያን በሀገሪቱ የተፈጠረውን ቀውስ በመሸሽ ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት ዝግጅቶቻቸውን ማጠናቀቃቸውን እና በጉዳዩ ዙሪያ የናይጀሪያ መንግስት ባወጣው መግለጫ ተማሪዎቹ በቤታቸው እንዲቆዩ እና ምንም አይነት እንቅስቃሴ እንዳያደርጉ ማሳቡም ተዘግቧል። ወደ ድንበር አከባቢ መጓዝ አደገኛ መሆኑን ያስጠነቀቀቅ በሱዳን የናይጀሪያ ኤምባሲ ዜጎቹን ለማስወጣት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልጾም ነበር።

ይሁን እንጂ የመንግስታቸውን ማስጠንቀቂያ ወደ ጎን ያሉ እና ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት የሞከሩ ናይጀሪያውያኑ በኢትዮጵያ በኩል መግባት ተከልክለው ድንበር ላይ እንደሚገኙ የሀገሪቱ መገናኛ ብዙሃን አስታውቀዋል። አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.