አዲስ አበባ፣ ግንቦት 24/2015 ዓ.ም፡- በፌደራል መንግስቱ እና በትግራይ ሀይሎች መካከል የሰላም ስምምነት ቢፈረምም አሁንም በምዕራብ ትግራይ የሚካሄደው የዘር ማጽዳት የወንጀል ተግባር እንደቀጠለ ነው ሲል ሂዩማን ራይት ወች ዛሬ ግንቦት 24 ቀን 2015 ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። በምዕራብ ትግራይ የሰብአዊ መብት ጥሰት የፈጸሙ አካላትም ለፈጸሙት ግፍ ተጠያቂ አልተደረጉም ሲል ተችቷል።
በምዕራብ ትግራይ የሚገኙ አስተዳደር አካላት እና የአማራ ሀይሎች ከሰላም ስምምነቱ በኋላም በምዕራብ ትግራይ የሚገኙ የትግራይ ተወላጆች ላይ የዘር ማጽዳት ተግባር እየፈጸሙ ነው ሲለ የኮነነው ተቋሙ የፌደራል መንግስቱ ወንጀሉን የፈጸሙ የጸጥታ ሀይሎችን እና የአከባቢው ባለስልጣናትን በማንሳት፣ በመመርመር እና ለፍርድ በማቅረብ ግዴታውን እንዲወጣ አሳስቧል።
የሰላም ስምምነቱ በምዕራብ ትግራይ የሚፈጸመውን የዘር ማጽዳት አላስቆመውም ሲሉ የሂዩማን ራይት ዎች የአፍሪካ ጉዳዮች ምክትል ዳይሬክተር ለታሺያ ባደር መናገራቸውን ያስነበበው መግለጫው የኢትዮጵያ መንግስት ተጎጂዎች ፍትህ እንዲያገኙ ለማድረግ ቁርጠኛ ከሆነ ገለልተኛ ምርመራን መቃወም የለበትም፣ ወንጀል ፈጻሚዎችም ተጠያቂ እንዲሆኑ ማድረግ አለበት ማለታቸውንም አካቷል። መግለጫው በተጨማሪም የኢትዮጰያ መንግስት በምዕራብ ትግራይ ወንጀል የፈጸሙ አካላትን ለፍትህ ለማቅረብ ምንም ፍላጎት የለውም ሲል ተችቷል።
በአለም አቀፍ ህግ መሰረት ከቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ መንደራቸው የመመለስ መብት አላቸው ያለው የሰበአዊ መበት ተቆርቋሪው ተቋም ሂዩማን ራይት ዎች ነገር ግን አሁናዊ የምዕራብ ትግራይ ሁኔታ ወደ ቀያቸው በፈቃደኝነት ለመመለስ ለሚፈልጉ የአከባቢው ተፈናቃዮች አመች አይደለም ሲል አስታውቋል። ተቋሙ ያነጋገራቸው ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው መመለስ እንደሚፈልጉ፤ ነገር ግን አሁንም በቦታው ያሉት ባለስልጣናት የግፍ ወንጀል ተግባራቸው በመቀጠላቸው ለመመለስ ፍቃደኛ አለመሆናቸውን ነግረውኛል ሲል በመግለጫው አካቷል።
ተቋሙ ባደረገው ምርመራ ከዚህ ቀደም በሰብአዊ መብት ጥሰት ተሳታፊ የነበሩት ኮለኔል ደመቀ ዘውዱ እና በላይ አያሌው የተባሉ ባለሰልጣናት አሁንም በአከባቢው በሚገኙ የትግራይ ተወላጆች ላይ በዘፈቀደ የማሰር፣ ግርፋት የመፈጸም እና በግዴታ ከቀያቸው የማፈናቀል ተግባር መቀጠላቸውን አመላክቷል።
ከነሃሴ 2014 እስከ ሚያዚያ 2015 ዓ.ም ድረስ ባለው ጊዜ የአይን እማኞችን፣ ተጠቂዎችን እና የእርዳታ ሰራተኞችን ያካተተ 35 ሰዎችን ማነጋገሩን ያስታወቀው መግለጫው የአከባቢው ባለስልጣናት እና የአማራ ሀይሎች በጉልበት በምዕራብ ትግራይ በሁመራ፣ ራውያን እና አደባይ ከተሞች የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ማጎራቸውን እንደነገሩት አስታወቋል። የአማራ ልዩ ሀይል እና የፋኖ አባላት በሁመራ እና ራውያን ከተሞች በርካታ የትግራይ ተወላጆችን በሚታወቁ እና በማይታወቁ እስር ቤቶች አጉረው እያሰቃዯቸው መሆኑንም ገልጿል።
ተቋሙ በምክረ ሀሳብነት ካቀረባቸው ነጥቦች ውስጥም በምዕራብ ትግራይ የሰብአዊ መብት ጥሰት ላይ ተሳታፊ ናቸው ተብለው የሚጠረጠሩ የፌደራል እና የክልል ባለስልጣናት ከሃላፊነታቸው እንዲታገዱ የሚለው ይገኝበታል። በኮለኔል ደመቀ ዘውዱ፣ ኮማንደር ደጀን ማሩ እና በላይ አያሌው ላይ ምርመራ እንዲካሄድም ጠይቋል።
ሂዩማን ራይት ዎች ግኝቶቹን በሙሉ ለኢትዮጵያ መንግስት ማስታወቁን እና ምንም አይነት ምላሽ አለማግኘቱንም አስታውቋል። አስ