ዜና፡ በመዲናዋ የጎዳና ላይ ሕፃናት በመንግስተ የፀጥታ ሃይሎች “በኃይል፣ በዘፈቀደና በሕገ-ወጥ አሠራር” በጅምላ እንደሚታፈሱ ኢሰመኮ አስታወቀ

ፎቶ- ዘጋርዲያን

አዲስ አበባ፣ 28/ 2015 ዓ.ም፡- የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና የጸጥታ አካላት ከከተማዋ በጎዳና ላይ የሚገኙ ሕፃናትን በኃይል፣ በዘፈቀደና ሕጋዊ ባልሆነ አሠራር በአፈሳ መልክ በማንሳት የተሟላ አገልግሎት በሌለበት አቃቂ ክፍለ ከተማ በሚገኘው የተሃድሶ ማዕከል እንዲቀመጡ እንደሚደረግ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

ኢሰመኮ በአዲስ አበባ ከተማ የጎዳና ላይ ሕፃናት በጅምላ ተይዘው የሚቆዩበትን ሁኔታ በተመለከተ ትላንት ባወጣው መግለጫ አብዛኛዎቹ ሕፃናት ለተለያየ ጊዜ መጠን በማቆያ ጣቢያ እንዲቆዩ እየተደረገ የሚለቀቁ መሆኑን በክትትል መረጋገጡንም ገልጧል፡፡

ኮሚሽኑ “ሕፃናትን ከጎዳና ላይ ማንሳት፣ በፈቃደኝነትና አስፈላጊ ሁኔታዎችን ሁሉ በማመቻቸት ነው መተግበር ያለበት” ሲል ገልፆ የኃይል፣ የዘፈቀደና ሕገ-ወጥ አሠራሮች ሊወገዱ እና ተገቢውን አገልግሎቶች መስጠት  ይገባል ሲል አሳስቧል፡፡

ኮሚሽኑ በመዲናዋ የሚከበሩ ሕዝባዊና ሃይማኖታዊ በዓላት እንዲሁም ዓለም አቀፋዊና አህጉራዊ ጉባኤዎች ጋር በተያያዘ በርካታ በጎዳና ላይ ያሉ ሕፃናት በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ከጎዳና ላይ እንዲነሱ በማድረግ ለተለያየ የጊዜ መጠን በአንድ ማቆያ ስፍራ እንዲቆዩ ስለሚደረጉበት ሁኔታና ስለሰብአዊ መብቶች አያያዝ በተመለከተ ክትትሉን ያደረገው ከጥር 9 እስከ 26 ቀን 2015 ዓ.ም. መሆኑን ገልጧል፡፡

የኢሰመኮ የሴቶችና የሕፃናት መብቶች ኮሚሽነር መስከረም ገስጥ በጎዳና ላይ ላሉ ሕፃናት ዘላቂ መፍትሔ የመቀየስ አስፈላጊነትን እና አስቸኳይነቱን አበክረው ገልጸው፤ “ሕፃናትን ከጎዳና ላይ ማንሳትና ተገቢውን አገልግሎቶች መስጠት በፈቃደኝነትና አስፈላጊ ሁኔታዎችን ሁሉ በማመቻቸት የሚተገበር እንጂ፤ በኃይል፣ በዘፈቀደ እና ሕገ-ወጥ በሆነ መንገድ ሊፈጸም ስለማይገባ ይህን ዓይነት የኃይል፣ የዘፈቀደና ሕገ-ወጥ አሠራር ሊወገድ ይገባል” ብለዋል፡፡

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.