ዜና፡ በመዲናዋ ሕግና መመሪያ ያላከበሩ 3ሺህ 800 አመራሮችና ባለሙያዎች ተጠያቂ ሆነዋል ተባለ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፐብሊክ ሰርቪስና ሰው ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሂክማ ከይረዲን

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 4/2015 ዓ.ም፡- በ2015 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት በአገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ ሕግና መመሪያ ያላከበሩ 3 ሺህ 800 አመራሮች እና ባለሙያዎች ተጠያቂ መሆናቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ አስታወቀ፡፡

በአገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ የታዩ ችግሮችን በመፈተሽ በአገልግሎት አሰጣጡ ከሕዝብ በቀረቡ ጥቆማዎች መሰረት በአድልኦ የሚሰሩ፣ በሌብነት የተጠረጠሩ፣ ሕዝብን ለእንግልት የዳረጉ 3 ሺህ 800 አመራርና ባለሙያዎች በተለያየ መንገድ ተጠያቂ መደረጋቸውን የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዘግቧል፡፡

ቢሮው 3 ሺህ 800 አመራርና ባለሙያዎች ተጠያቂ መደረጋቸውን ከመግለፅ በተጨማሪ የአማራሮቹና ባለሞያዎቹን ማንነት አልገለፀም፡፡

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፐብሊክ ሰርቪስና ሰው ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሂክማ ከይረዲን በከተማዋ 47 አገልግሎት ሰጪ ተቋማት መኖራቸውን ጠቁመው ከተማ አስተዳደሩ በከተማዋ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር እንዳይኖር፣ አገልግሎቶች ፍትሐዊ፣ ውጤታማና ቀልጣፋ እንዲሆኑ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የቢሮው ሃላፊዋ ይህን ያሉት የከተማዋ ተቋማት ለነዋሪዎች በሚሰጡት አገልግሎት ዙሪያ ትናንት ከነዋሪዎችና ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር ባደረጉበት መድረክ ሲሆን ሌብነትና ብልሹ አሰራርን መከላከል፣ የተለያዩ ግብዓቶችን ማሟላት፣ ምቹ ስራ አካባቢን መፍጠርና የተገልጋይ እርካታን መመዘን ላይ ትኩረት ያደረገ ስራ በቀጣይ እንደሚከናወንም ተናግረዋል ተብሏል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፐብሊክ ሰርቪስና ሰው ሀብት ልማት ቢሮ የከተማ አስተዳደሩን ተቋማት አፈጻጸም በመገምገም ማሻሻያዎች እንደሚያደርግ ጠቁመዋል።

በተጨማሪም ከአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ጋር በመተባበር በየሳምንቱ የሬዲዮና የቴሌቪዥን የቀጥታ ፕሮግራሞችን በማዘጋጀት የተቋማት አመራሮች ከሕዝብ በሚቀርቡላቸው ጥያቄዎች ላይ ምላሽ እንዲሰጡም እያደረገ መሆኑን አስረድተዋል።

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.