አዲስ አበባ፣መስከረም 5 2015 ዓ.ም፡- የአውሮፓ ህብረት ትናንት ማምሻውን በሰጠው መግለጫ “በትግራይ ክልል ርዕሰ መዲና በሆነችው መቀሌ ላይ መስከረም 3 እና 4 2015 ዓ.ም የተፈፀመው ሁለት ሰው አልባ አውሮፕላን የአየር ድብደባ “የኢትዮጵያን ጭላጭል የሰላም ተስፋ አደጋ ላይ ይጥላል” ሲል ገልጿል።
የአውሮፓ ህብረት መግለጫ የወጣው ባለፈው ረቡዕ መስከረም 4 ቀን በመቀሌ ከተማ በዳግም አምሳል በተባለው አካባቢ ሁለት ሰው አልባ አውሮፕላኖች በፈጸሙት ጥቃት 10 ንፁሀን ዜጎች ሲሞቱ 14 ሰዎች ቆስለዋል ሲሉ የአይደር ኮምፕረሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ዋና ስራ አስፈፃሚ፣ የልብና የደም ህክምና እና የቀዶ ህክምና ተባባሪ ፕሮፌሰር ፣ በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የደረት ቀዶ ጥገና ሐኪም የሆኑት ክብሮም ገብረስላሴ ከተናገሩ በኋላ ነው፡፡
ከክልሉ ጋር ግንኙነት ያለው ሚዲያው እእንደዘገበው ባሳለፈው ማክሰኞ እለት በተፈጸመ ተመሳሳይ የአየር ድብደባ በአካባቢው የሚገኘውን ድምጺ ወያነ የስርጭት መስመሮች ላይ ውድመት በማድረስ መደበኛ ስራውን በማቆም ወደ ጊዜያዊ ስቱዲዮ እንዲዘዋወር አስገድዶታል። በሌላ የአየር ጥቃትም በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ አዲ-ሀኪ ካምፓስ ላይ ጉዳት መድረሱን ዩኒቨርሲቲው አስታውቋል።
ስለሁለቱም ሰው አልባ አውሮፕላን የአየር ድብደባ የፌደራል መንግስት እስከአሁን ድረስ የሰጠው መግለጫ የለም።
የአውሮፓ ህብረት “እንደገና ከተቀሰቀሰው ጦርነት በኋላ የሰብአዊ ዕርዳታ አቅርቦቶች መዘጋታቸው በሲቪል ህይወት ፣ በኢኮኖሚ እና በሀገሪቱ እድገት ላይ ከፍተኛ እና ከባድ ኪሳራን እንደሚጨምር” አስጠንቅቋል ። አክሎም የኤርትራ ሚና የኢትዮጵያን ቀጣይ የሰላም ጥረት ማደናቀፉን ቀጥሏል ብሏል።
ከአፍሪካ ህብረት እና ከአሜሪካ መንግስት በተጫማሪም የትግራይ ክልል መንግስት እሁድ መስከረም 1 ቀን 2015 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ “በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት በተጠናከረ የሰላም ሂደት ላይ ለመሳተፍ መዘጋጀቱን እንዲሁም ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር በአፋጣኝ እና በጋራ ስምምነት በማድረግ ግጭቶችን ለማስቆም” ፈቃደኛ መሆኑን ማሳወቁን ቀድመው እውቅና ከሰጡ አካላት መካከል የአውሮፓ ህብረት አንዱ ነው፡፡
መግለጫው “ጦርነትን ለማስቆም፣ በድርድር ዘላቂ የሆነ የተኩስ አቁም ስምምነት ለመመስረት እና ቀጥታ ውይይት ለማድረግ እድል መፍጠር ነበረበት” ሲል የአውሮፓ ህብረት ገልጾ “የሰላም ውይይቶች የቀጣይ ብቸኛ መንገድ ናቸው” ብሏል። አዲሱን የኢትዮጵያ አመት ሰላማዊ ለማድረግ ጊዜ መጥፋት የለበትም ስልም አክሏል።
የአውሮፓ ህብረት የፌደራልም ሆነ የትግራይ መንግስታት ይህንን እድል ተጠቅመው ጦርነቱን እንዲያቆሙ እና በድርድር ዘላቂ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እንዲደርሱ እንደሚያበረታታ እና “በአፍሪካ ህብረት የሚመራውን ሂደት እንደሚደግፉ እና ከአለም አቀፍ አጋሮች ጋር በመቀናጀት በንቃት ለመሳተፍ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጿል።አስ