አዲስ አበባ፣ሰኔ 19/2015 ዓ.ም፡- በሕገወጥ የወርቅ ምርት፣ ግብይትና ዝውውር ተሳትፎ ነበራቸው የተባሉ 32 የመንግሥት ኃላፊዎች፣ የጸጥታ መዋቅር አመራሮችና አምራቾች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አስታወቀ፡፡
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለመገናኛ ብዙኃን በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው በቁጥጥር ስር የዋሉት ግለሰቦች በሕገወጥ መንገድ ወርቅ ሲያመርቱ፤ ሲያዘዋውሩ፣ በጥቁር ገበያ ሲሸጡ እንዲሁም ከውጭ ሀገራት ዜጎች ጋር የጥቅም ትስስር በመፍጠር ብሔራዊ ጥቅምን በሚጎዳ ዕኩይ ተግባር ላይ ተሰማርተው የተገኙ ናቸው፡፡
በቁጥጥር ስር ከዋሉት 32 ግለሰቦች መካከል ስምንቱ የመንግሥትና የጸጥታ መዋቅር አመራሮች ሲሆኑ፤ ሰባቱ ደግሞ ሕጋዊ ፈቃድን ሽፋን አድርገው በሕገወጥ መንገድ ሲሠሩ የነበሩ አምራቾች እንዲሁም 17 አዘዋዋሪዎችና በሕገወጥ ድርጊቱ የተለያየ ተሳትፎ ያላቸው መሆናቸው ተገልጿል፡፡
በዚህ መሰረትም ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የኩምሩክ ወረዳ ገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ፅ/ቤት ኃላፊ ከማል መሀመድ፣ የግብርና ፅ/ቤት ኃላፊ አብዱልከሪም ዬሚዳ፣ የወረዳው ፖሊስ አመራር ም/ኮ አብዱልሙንየም ሱሌማን እንዲሁም ምክትል አስተዳዳሪ የነበረው አሳይድ አልዕግብ በቁጥጥር ውለዋል፡፡
በጋምቤላ ክልልም የዲማ ወረዳ ማዕድን ፅህፈት ቤት ኃላፊ የሆነው ኡቦንግ ኡቶው ኡጉድ እንዲሁም በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የምዕራብ ኦሞ ዞን የቤሮ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ከበደ ቡርጂ እና ሌሎችም ከሕገወጥ ድርጊቱ ጋር ትስስር የነበራቸው ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ሥር ሲውሉ 21 ክላሽንኮቭ ጠመንጃ ከ420 መሰል ጥይቶች፣ 14 ሽጉጦች ከ62 መሰል ጥይቶች፣ 2 ኤፍ1 ቦምቦች፣ 250 የብሬን ጥይቶች፣ ወርቅ፣ 8 የወርቅ ሚዛን፣ 5 የወርቅ መፈተሻ ማሽን፣ 2 የወርቅ ማቅለጫ እንዲሁም የተለያዩ የወርቅ ናሙናዎች፣ ኬሚካሎች እንዲሁም በርካታ የተለያዩ ሀገራት ገንዘቦችና የባንክ ደብተሮች በኤግዚብትነት መያዛቸው ታውቋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ከ15 ቀን በፊት በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል በሕገወጥ የወርቅ ምርትና ግብይት ተግባር ተሰማርተው የተገኙ 29 የውጭ ሀገራት ዜጎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ይታወሳል፡፡አስ