አዲስ አበባ፣ መጋቢት 29/ 2015 ዓ.ም – የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ በመግባት በጋምቤላ እና ቤኒሻንጉል ክልል የወርቅና የተለያዩ ማዕድናት ፍለጋ ላይ የተሰማሩ ከዘጠና በላይ የውጭ ሀገር ዜጎችና ኢትዮጵያውያን ተባባሪዎቻቸው በቁጥጥር ሥር ማዋሉን አስታወቀ።
ግብረ ኋይሉ የየት ሀገር ዜጎች መሆናቸውን ያልገለጻቸው በህገወጥ መንገድ ወደ ሀገር ውስጥ መግባታቸውን አመላክቶ ህገወጥ ስራ ሲሰሩ እንደነበር በፌደራል ፖሊስ የማህበራዊ ትስስር ፌስቡክ ገጽ ላይ ያወጣው መረጃ አስታውቋል።
በዚህም መሰረት የፀና የጉዞ ሰነድ፣ የመግቢያ ቪዛ እንዲሁም የመኖሪያ ፍቃድ ሳይኖራቸው በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ ገብተው በጋምቤላ ክልል በሕገ-ወጥ የወርቅና የተለያዩ ማዕድናት ፍለጋ ላይ የተሰማሩ 45 የውጭ ሀገር ዜጎች እና ሦስት ኢትዮጵያውያንን ከነ-ኤግዚቢቱ በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እየተካሄደባቸው እንደሚገኝ ተጠቁሟል።
በተመሳሳይ ሁኔታ የፀና የጉዞ ሰነድ፣ የመግቢያ ቪዛ እንዲሁም የመኖሪያ ፍቃድ ሳይኖራቸው በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ ገብተው በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በሕገ-ወጥ የወርቅና የተለያዩ ማዕድናት ፍለጋ እንዲሁም የማምረት ስራ ላይ የተሰማሩ 47 የውጭ ሀገር ዜጎች፣ ዘጠኝ ኃላፊነታቸው የተወሰነ የግል ማኅበራት እንዲሁም ሰባት ኢትዮጵያውያን ግለሰቦችን ከእነ-ኤግዚቢቱ በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው እንደሚገኝም ተገልጿል።
የጋራ ግብረሃይሉ እንዳስታወቀው ወንጀለኞቹን በቁጥጥር ስር ያዋለው ከማህበረሰቡ በደረሰው ጥቆማ እና ባካሄደው ጠንካራ ክትትል መሆኑን አመላክቷል። በተጨማሪም ተጠርጣሪዎቹ በህገወጥ መንገድ ወደ ሀገር ውስጥ መግባት ብቻ ሳይሆን የማዕድን ምርቱንም በህገወጥ መንገድ ከሀገር በማስወጣት ከሁለቱ ክልሎች መገኘት የሚገባው ገቢ እንድታጣ አድርገዋል ሲል ገልጿል። የጋራ ግብረሃይሉ መሰል የወንጀል ተግባራችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ኅብረተሰቡ ከፀጥታ አካላት ጋር ተገቢውን ቅንጅት በማድረግና ጥቆማ በመስጠት እያደረገ ያለውን ቀና ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪውን አቅርቧል።
ክትትሉ በጋምቤላ እና በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ብቻ ተወስኖ እንደማይቀር እና በሌሎች ክልሎችም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይሉ ማስታወቁን መረጃው አካቷል።