ፀጋ በላቸውና ክንስታብል የኋላማብራት ወ/ማርያም
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 22/2015 ዓ.ም፡- በሲዳማ ክልል ዋና ከተማ በሆነችው ሀዋሳ ግንቦት 15 2015 ፀጋ በላቸው የተባለች ወጣት በከተማው ከንቲባ ጥበቃ ክንስታብል የኋላማብራት ወ/ማርያም ተጠልፋ እስካሁን የት እንዳለች ማወቅ አልተቻለም፡፡
በሀዋሳ ከተማ የዳሸን ባንክ ሰራተኛ የሆነው ፀጋ በላቸው ማክሰኞ ግንቦት 15 ቀን ስራዋን አጠናቃ ወደ መኖርያ ቤቷ በማምራት ላይ እያለች መነኃሪያ ክፍለ ከተማ ስትደርስ ኮንስታብል የኋላማብራት ወ/ ማርያም በተባለ የሀዋሳ ከንቲባ ጠባቂ ተጠልፋ ወዳልታወቀ ቦታ መወሰዷን ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተለ የሚገኝ የቤተሰቧ አባል ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጧል፡፡
“ማክሰኞ ማታ ወደ ቤቷ አለመግባቷን አከራይዋ ነገረችን፤ ጠዋት ወደ ስራ ቦታዋ ስንሄድም እዛ የለችም፤ አብራት የምትሰራ የባንኩ ሰራተኛ በከንቲባው ጠባቂ መጠለፏን ስታወራ ሰማናት” በማለት ይህ የቤተሰቧ አባል ገልጧል፡፡
“ይህ የጠለፋት ግነሰብ ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ያለፍላጎቷ እንደሚያገባት ሲዝትባት እንደነበር” የገለፀው የቤተሰቡ አባል፣ ጠላፊው የፖሊስ አባል አንደነበር እና አሁን ላይ የከንቲባው ጠባቂ በመሆን በመስራት ላይ እንዳለ፣ እንዲሁም ወንጀሉን የሰራው የአመት እርፍት ወስዶ መሆኑን አስረድቷል፡፡
“መጠለፏን ካወቅን በኋላ ወድያውኑ ወደ ለከተማው ፖሊስ ጣቢያ እና ለሲዳማ ክልል ፖሊስ ብናሳውቅም ጉዳዩ አንዳሰብነው ትኩረት አልተሰጠውም፤ ግለሰቡ ከፖሊሶች ጋር ግኑኝነት ስላለው ውስጥ ያሉት ፖሊሶች ጉዳዩ ትኩረት እንዳያገኝ እያደረጉ ያሉ አሉ፤ የአካባቢው ባህል ነው በሚል ዝም እንድንል የሞከሩም አሉ ሲል” አክሎ ገልጧል፡፡
ፀጋ ከተጠለች በኋላ በአንድ ሳምንት ውስጥ ይርጋለምና ሀገረ ሰላም ከተማን ጨምሮ ወደ ተለያዩ ቦታዎች መወሰዷን መረጃ 㙀ንዳለቻ የገለፀው ይህ ግለሰብ አሁን ግን የት አንዳለች አናውቅም ሲል ተናግሯል፡፡ “ ብዙ ግዜ ፖሊሶች ታይቷል የተባለበት ቦታ እሱን ፍለጋ ሰሲሄዱ ውስጥ ያሉት ፖሊሶች መረጃውን ለእሱ በማሳወቅ እንዲያመልጥ ያደርጋሉ” ሲል ተናግሯል፡፡
ፍቃዱ( ለደህንነቱ ሲባል ስሙ የተቀየረ) ለፀጋ ቤተሰቦች ቅርበት ያለው ሰው ሲሆን ለአዲስ ስታንዳርድ እድገለፀው ፀጋ በእምነቷ አስተምሮ መሰረት ለማግባት የቤት ክርስቲያንን የጋብቻ ትምህርት ከእጮኛዋ ጋር ተምረው ጨርሰዋል፡፡
የሲዳማ ክልል ደህንነት ቢሮ ኃላፊ አለማየሁ ጢሞትዮስ ፀጋ ግንቦት 15 በክንስታብል የኋላማብራት መጠለፏን ከከተማው የደህንነት ካሜራ ማረጋገጣቸውን ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጠዋል፡፡
“የፀጋን የመጠለፍ መረጃ ከደረሰን በኋላ ከፍተኛ ክትትል እያደረግን ነው ያለነው” ያሉት ኃላፊው በአሁኑ ሰዓትም ከአንደኛ ተጠርጣሪው ጋር ይህንን ድርጊት የፈፀሙ እና ከዛ በኋላም ከውስጥ መረጃ ሲያቀብሉ የነበሩ ስድስት ተጠርጣሪ ፖሊሶችን በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን ገልፀዋል፡፡ አክለውም እየተደረገ ባለው ክትትል ግለሰቧን የወሰደበትን ቦታ እናውቃለን ሲሉ ገልፀው ኮንስታብል የኋላማብራትን በቁጥጥር ስር ለማዋል እየሰራን ነው ብለዋል፡፡
ፀጋ በላቸው ተወልዳ ያደገችው በወልቂጤ ከተማ ሲሆን ከጅማ ዩኒቨርሲቲ በአካውንቲንግ የመጀመርያ ዲግሪዋን ካጠናቀቀች በኋላ ከ2014 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ አሁን በሃዋሳ ከተማ ዳሸን ባንክ ዋርካ ቅርንጫፍ ተቀጥራ በመስራት ላይ እንደነበረች የቅርብ ቤተሰቦቿ ለአዲስ ስታንዳርድ ገልፀዋል፡፡ አስ