በትግራይ ክልል የሚገኙ አባቶች
አዲስ አበባ፣ ሓምሌ 27/ 2015 ዓ.ም፡- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የዶግማ፣ የቀኖናና የአስተዳደራዊ ጥሰቶችን ፈፅመዋል ያላቸው አራት ሊቃነ ጳጳሳትን፣ ዘጠኝ ተሸዋሚዎችንና “ሂደቱን አስተባብረዋል” ያላቸውን አባቶች ላይ የውገዘት ውሳኔ ማስተላለፉን አስታወቀ፡፡ የትግራይ አባቶች በበኩላቸው ውግዘቱ ቅቡል አይደለም ሲሉ ገልፀዋል፡፡
ይህንን ተከትሎ በትግራይ የሚገኙ አባቶች ዛሬ ሀምሌ 27 ባወጡት መግለጫ ቅዱስ ሲኖዶሱ ያስተላለፈው የውግዘት ውሳኔ ተቀባይነት የሌለው ሲሉ አጣጥለውታል፡፡ “በጉዟችን ላይም ምንም ተፅእኖ የለውም ” ሲሉም ገልፀዋል።
ቅዱስ ሲኖዶሱ ሐምሌ 26 ቀን 2015 ዓ.ም. ባካሄደው አስቸኳይ ምልዓተ ጉባኤ፣ ብፁዕ አቡነ ኢሳይያስ የመቀሌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የእንቅስቃሴው ሰብሳቢ፣ ብፁዕ አቡነ መቃርዮስ በክልል ትግራይ የማዕከላዊ ዞን አክሱም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ብፁዕ አቡነ መርሐ ክርስቶስ የአዲግራት ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ የሽሬ እንዳሥላሴ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስን ከዱቁና ጀምሮ ያለው ሙሉ ሥልጣነ ክህነት በመሻር፣ በቤተ ክርስቲያናችን መንፈሳዊ አገልግሎት ዙርያም በሕይወትም ሆነ በሞት ማናቸውንም መንፈሳዊ አገልግሎት እንዳያገኙ ማውገዙን አስታወቋል፡፡
ቅዱስ ሲኖዶስ ሊቃነ ጳጳሳቱን ያወገዘው ሐምሌ 16 እና 23 ቀን 2015 ዓ/ም በክልል ትግራይ በማእከላዊ ዞን አክሱም የቤተ ክርስቲያንን ቀኖና በመጣስ ባልተሰጣቸው ስልጣን በትግራይ 9 ኤጴስ ቆጰሳትን በመሾማቸው፣ ሲኖዶስ በማቋቋማቸው የቀኖና ቤተ ክርስቲያን ጥሰት በመፈፀማቸው መሆኑን ትላንት ሓምሌ 26ባወጣው መግለጫው ገልጧል፡፡
በተጨማሪም ሹመቱን በሰጡት አራት ሊቃነ ጳጳሳት የኤጲስ ቆጶስነት ሹመት አግኝተናል ተሹመናል ያሉት 9 መነኮሳት ማለትም አባ ዘሥላሴ ማርቆስ፣ አባ ኃይለ ሚካኤል አረጋይ፣ አባ እስጢፋኖስ ገብረ ጊዮርጊስ፣ አባ መሓሪ ሀብቶ፣ አባ ኤልያስ ታደሰ ገብረ ኪዳን፣ አባ ጽጌ ገነት ኪዳነ ወልድ፣ አባ ዘርአ ዳዊት ብርሃነ፣ አባ ዮሐንስ ከበደና አባ የማነ ብርሃን ወልደ ሳሙኤል፤ ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን በመጣሳቸው ከዲቁና ጀምሮ ያለው ሙሉ ሥልጣነ ክህነት ተሽሮ በቤተ ክርስቲያናችን መንፈሳዊ አገልግሎት ዙርያ በሕይወትም ሆነ በሞት ማናቸውንም መንፈሳዊ አገልግሎት እንዳያገኙ ውሳኔ ማሳለፉን ቅዱስ ሲኖዶስ አስታውቋል፡፡
ሊቃነ ጳጳሳቱ ሥልጣነ ክህነታቸውና የማዕረግ ስማቸው በምልዐተ ጉባኤ ውሳኔ ተነስቷል ያለው ቅዱስ ሲኖዶሱ ከሐምሌ 26 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ በቀድሞ ዓለማዊ ስማቸው ይጠራሉ ብሏል፡፡
“ይህ ህገወጥ ሢመት እንዲፈጸም ከመጀመሪያው ጽንሰ ሀሳብ ጀምሮ መሪ ተዋናይና ቀስቃሽ በመሆን ኢትዮጵያን ኤልዛቤል በማለትና ስሟን የሚጠራ የተረገመ ይሁን በማለት እንዲሁም ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ጋር የዶግማ ልዩነት አለን በማለት የኑፋቄ ትምህርት በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን የተናገሩትና በህገወጥ ሢመቱ ላይም በእጩነት ተመርጠው በሂደት ላይ ያሉት አባ ሠረቀ ብርሃን ወልደ ሳሙኤልና ሂደቱን በዋና አስፈጻሚነት በመምራትና መግለጫ በመስጠት ላይ ያሉት መ/ር ተስፋዬ ሐደራ ከዛሬ ሐምሌ 26 ቀን 2015 ዓ/ም ጀምሮ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ተወግዘው ከቤተክርስቲያን ተለይተዋል” ሲልም መግለጫው አክሏል።
የተወገዙት ግለሰቦች በሙሉ በሠሩት የቀኖና ጥሰት ተጸጽው ይቅርታን ቢጠይቁ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በቀኖና ቤተ ክርስቲያን መሠረት የምትቀበላቸው መሆኑን ቅዱስ ሲኖዶስ በመግለጫው ገልጧል፡፡
“መንበረ ሰላማ” የሚለው ሥያሜን በተመለከተ በቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ትውፊትም ሆነ በቀደምት አብያተ ክርስቲያናት ትውፊት የማይታወቅ፣ ሕገወጥ ፣ ሃይማኖታዊ መሠረት የሌለው፣ ከቀኖና የወጣ፣ አስተዳደራዊ መዋቅርን የሚያዛባ በመሆኑ የኢትዮጵያ ኦርቶዶከስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አትቀበለውም ተብሏል፡፡
“ይህን ህገወጥ ተግባር ለመፈጸም በሀገራችን ተከስቶ የነበረው ጦርነት እንደ ምክንያት የተጠቀሰ መሆኑን የገለፀው ቅዱስ ሲኖዶሱ ቤተክርስቲያን ከጦርነቱ በፊት ጦርነት እንዳይከሰት ያደረገችውን ጥረት በጦርነቱ ወቅት ለተደረጉ ድጋፎችና ከጦርነቱ በኋላ ለተደረጉ የእንወያይ ጥረቶች እንዲሁም በቤተክርስቲያን በኩል የተዘረጋውን የሰላምና የእርቅ በር ይልቁንም ለሰላም ሲባል በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባዔ የተጠየቀውን ይፋዊ ይቅርታ በመግፋት የተደረገ ኢ-ክርስቲያናዊ ተግባር ነው” ብሎታል።
የትግራይ አባቶች በመግለጫቸው ሲኖዶሱ በትግራይ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን መንበረ ሰላማ ቤተክህነት ብፁኣን ኣበው ፣ ሊቃነ ጳጳሳት ፣ ኤጲስ ቆጳሳት እና አገልጋዮች ላይ አስተላለፍኩት ያለው ውግዘት ከንቱ እና ቅቡሉነት የሌለው ነው ብለዋል፡፡ አባቶቹ ” ይህ ከንቱ ውግዘት የመንበረ ሰላማ ጉዞ ላይ ምንም አይነት ተፅእኖ እንደሌለው እና ለአፍታም ቢሆን የሚቆም ነገር እንደሌለ እንገልፃለን ” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። አስ