ዜና፡ ቅዱስ ሲኖዶስ ለፆመ ነነዌ ህዝበ ክርስቲያኑ ጥቁር ልብስ በመልበስ እንዲፆም ጥሪ አቀረበ

አዲስ አበባ፣ ጥር 26/2015 ዓ.ም፡- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ህዝበ ህርስቲያኑ፣ መንግስት ድጋፍ የሚሰጠውንና መፈንቅለ ሲኖዶስ ለማድረግ የሞከረውን ህገ- ወጡን ቡድን በመቃወም ከጥር 29 እስከ የካቲት 1 ቀን 2015 ዓ.ም የሚቆውን ጾመ ነነዌን ጥቁር ልብስ ብቻ በመልበስ በጾምና በጸሎት ምሕላ በመያዝ እንዲያሳልፍ ጠየቀ፡፡

ጾመ ነነዌን ምክንያት በማድረግ በመላው ዓለም የሚገኙ ሕዝበ ክርስቲያን ጥቁር ልብስ ብቻ በመልበስ በጾምና በጸሎት ምሕላ በመያዝ በቤተ ክርስቲያን ዓውደ ምሕረት በመገኘት ወደ እግዚአብሔር ጾም፤ ጸሎትና ምሕላ እንድታቀርቡ ጥሪ ተላልፏል፡፡ጥቁር ልብስ የምንለብሰው በመከራ መጽናት ለመግለጽ ነው ሲል መግለጫው ገልጧል፡፡

ጾሙን ጥቁር ልብስ በመልበስ እንዲታለፍ የጠየቀው መግለጫ ቅዱስ ሲኖዶሱ የኦሮሚያ እና ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቅዱስ ሲኖዶስ በማድረግ እራሳቸውን የሾሙት እነዚህ ሕገወጥ ቡድኖች ከድርጊታቸው ሊታቀቡ ካለመቻላቸውም በላይ በመንግሥት ኃይሎች በመታገዝ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የምታስተዳድራቸውን መንበረ ጵጵስናዎችንና ቢሮዎችን በኃይል በመውረርና በመስበር ከፍተኛ ጥፋት እያደረጉ ይገኛሉ ብሏል፡፡

ሲኖዶሱ መንግሥት ሕግ ከማስከበር ይልቅ ለሕገ ወጥ ቡድኖች ድጋፍ በመስጠት የቤተ ክርስቲያኒቱን ሕግና መብት ሊያስከብር ስላልቻለ ሁሉን ማድረግ ወደሚቻለው አምላካችን በመማፀን ጸሎትና ምሕላ ማድረጉ አስፈላጊ መሆኑን ቅዱስ ሲኖዶስ ተረድቷል ብሏል።

ጥር 24 የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ መንግሥት በሕገ መንግሥቱ የተጣለበትን ኃላፊነት በመወጣት የቤተ ክርስቲያኒቱን ተቋማዊ ልዕልና እንዲያስጠብቅ እንዲሁም ህገ ወጡን ድርጊት ተገቢውን እርምት እንዲሰጥ አሳስቦ ይህ የማይሆን ከሆነ ግን ከቅዱስ ፓትርያርኩ ጀምሮ ብፁዓን አበው ሊቃነጳጳሳት፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ አገልጋይ ካህናትና ምእመናን ጭምር የሚሳተፉበት ሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ሰላማዊ ሰልፍ እንደሚካሄድ አስታቋል፡፡

የቅዱስ ሲኖዶሱ ተቃውሞ የቀጠለ ሲሆን አዲስ የተሸሙት ሊቀ ጳጳስ 25ቱን ተሸዋሚዎችን ወደ ተለያዩ የኦሮሚያ ክልል አገረ ስብከት መላክ ቀጥለዋል። የምዕራብ አርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሆነው የተሸሙት ብፁዕ አቡነ ጳውሎስ በሳምንቱ መጨረሻ ወደ ሻሸመኔ ከተማ እንደሚጓዙ መረጃዎች ጠቁመዋል።

የኦሮሚያና ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቅዱስ ሲኖዶስ ትላንት በተሰጠው መግለጫ  ከዚህ ሳምንት መጨረሻ ጀምሮ በቀሪዎቹ የኦሮሚያ አካባቢዎች እና በደቡብ ክልል በሚገኙ አህጉረ ስብከትም እንደሚቀጥል ገልጧል፡፡

ባሳለፍነው ሳምንት ወደ ምዕራብ ወለጋ እና ቄለም ወለጋ አገረ ስብከት የተላኩት ኤጴስ ቆጶሳት በመንገዳቸውና በመዳረሻቸው ደማቅ አቀባበል ተዶርጋላቸዋል ሲሉ ቃል አቀባዩ ገልፀዋል፡፡አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.