አዲስ አበባ፣ ግንቦት 16/2015 ዓ.ም፡- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል በተፈጠረው ጦርነት ምክንያት በትግራይ ክልል የሚገኙ ወገኖቻችን ያሉበትን ከፍተኛ ችግር ታሳቢ በማድረግ አስቸኳይ የሆነ ሰብአዊ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው በመሆኑ ሃያ ሚሊየን ብር ድጋፍ እንዲደረግ ሲል ወሰነ፡፡
ቅዱስ ሲኖዶሱ ይህን የወሰነው ከግንቦት 1 ቀን 2015ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ዛሬ ግንቦት 16 ቀን 2015 ዓ.ም. ሲያካሄድ የቆየውን የርክበ ካህናት ምልዓተ ጉባኤ አጠናቆ ባወጣው መግለጫ ሲሆን በስብሰባው የተለያዩ ውሳኔዎችን አስተላልፏል፡፡
በዚህም መሰረት በትግራይ አስቸኳይ ሰብአዊ እርዳታ ለሚሹ ሃያ ሚሊየን ብር ድጋፍ እንዲደረግ እንዲሁም መቀሌ የሚገኘው የቅዱስ ፍሬምናጦስ አባ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን መንፈሳዊ ኮሌጅ የሠራተኞችን ደመወዝና የሥራ ማስኬጃ በጀት እንዲለቀቅና በ2016 በጀት ዓመት ተማሪዎችን በመቀበል መደበኛ የሆነ የመማር ማስተማሩ የሥራ ሂደት እንዲቀጥል ቅዱስ ሲኖዶስ መመሪያ ሰጥቷል፡፡
በተጨማሪም በትግራይ ክልል በሚገኙት አህጉረ ስብከት ተቋርጦ የነበረው መንፈሳዊና አስተዳደራዊ ግንኙነትን በተመለከተ በቅዱስ ሲኖዶስ ተሠይሞ በሥራ ላይ የሚገኘው ልዑክ የጀመረውን እንቅስቃሴ እንዲቀጥል የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላትን በማነጋገር ተልዕኮውን እንዲፈጽም ምልዓተ ጉባኤው መመሪያ መሰጠቱ በመግለጫው ተገልጧል፡፡
በኦሮምያ ክልል በሚገኙ አህጉረ ስብከት ተፈጥሮ በነበረው ወቅታዊ ችግር ምክንያት በአህጉረ ስብከትና በአብያተ ክርስቲያናት አገልግሎት ስለተቋረጠ፣ ችግሮች እንዲቀረፉና ወደ መደበኛው የአሠራር መዋቅር እንዲመለስ ሰባት ሊቃነ ጳጳሳትን በመሠየም ከፌዴራልና ከኦሮምያ ክልላዊ መንግሥት ጋር በመወያየት ችግሮች እንዲፈቱ እንዲደረግ ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ አሳልፏል፡፡
ሢመተ ኤጲስ ቆጶሳትን በተመለከተ ክፍት በሆኑና በተደራቢነት በተያዙ፣ ጉልህና አንገብጋቢ ችግር ባለባቸው በኦሮምያ ክልልና በደቡብ ክልል ባሉ አህጉረ ስብከት ላይ 9 ኤጲስ ቆጶሳት እንዲሾሙ አስመራጭ ኮሚቴ ተሰይሟል ያለው መግለጫው ወደፊትም ተደርበው በተያዙና አስፈላጊ በሆኑ አህጉረ ስብከት እንደአስፈላጊነቱ በመንበረ ፓትርያርክ ተጠንቶ እንዲቀርብ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል ብሏል፡፡
በወቅታዊ ችግር ምክንያት በመላው ሀገራችን ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖቻችን ሁሉ በአጠቃላይ ችግሮቹን በጥናት በመለየት፣ ቤተ ክርስቲያናችን ምእመናን ልጆቿን በማስተባበር ሁለንተናዊ ሰብዓዊ ድጋፍ፣ የማጽናናትና የመጎብኘት መርሐ-ግብሮች እንዲደረጉ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡
በመጨረሻም ቤተ ክርስቲያኒቷ በሀገራችን በአንዳንድ ቦታዎች የሚታዩትን አላስፈላጊ ግጭቶች የዜጐች መፈናቀል፣ ስደት ተወግዶ ሁሉም ዜጋ በሀገሩ በእኩልነት፣ በሰላምና በፍቅር ተከባብሮ በአንድነት እንዲኖር፤ ለማድረግ ግጭቶችና አለመግባባቶች በውይይት እንዲፈቱ የሰላም ጥሪዋን አስተላልፋለች፡፡
በትግራይ የሚገኘው የመንበረ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን ሊቃነ ጳጳሳት 10 ኢጲስ ቆጶሳትን በትግራይ እና በውጭ ለመሾም መዘጋጀታቸውን በትላንትናው እለት ግንቦት 14 በሰጡት መግለጫ ማስታወቃቸው ይታወሳል፡፡