አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 5/2015 ዓ.ም፡- በአማራ ክልል በርካታ ከተሞች የክልሉ ልዩ ኃይል እንደገና ለማደራጀት በሚል የተወሰነው ውሳኔን በመቃወም ሲካሄዱ የነበሩ ሰልፎች እና ግጭቶች በዛሬው እለት ጋብ ማለቱንና መደበኛ እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውን ነዋሪዎች አስታወቁ። በተለይ በቆቦ፣ ደብረብርሃን እና ባህርዳር አንጻራዊ ሰላም እንደሰፈነባቸው ነዋሪዎቹ ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጸዋል።
በአማራ ክልል የፌደራል መንግስት የክልል ልዩ ኀይልን አፍርሶ በሌሎች መዋቅሮች ለማደራጀት እንቅስቃሴ መጀመሩን ተከትሎ በተደረገ የተቃውሞ ሰልፎች በነዋሪዎች እና በመካላከያ ሰራዊቱ እንዲሁም በልዩ ሀይሉ ወታደሮች እና በመከላከያ ሰራዊቱ መካከል ግጭቶች መስተናገዳቸው ይታወሳል። በግጭቶቹም የሰው ህይወት ማለፉን እና የአካል መጉደል ማስከተሉም ተዘግቧል።
በባህርዳር እና ደብረብርሃን በዛሬው እለት ሰላማዊ እንቅስቃሴ መኖሩን ነዋሪዎች ለአዲስ ስታንዳርድ አረጋግጠዋል። ባሕርዳር ከተማ ፍፁም ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንቅስቃሴ እያደረገች ነው ሲል የክልሉ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ በይፋዊ የማህበራዊ ትስስር ፌስቡክ ገጹ ባሰራጨው መረጃ አስታውቋል። ወቅታዊ ሁኔታዎችን በአልተገባ መንገድ በመተርጎም በክልል ደረጃ እንቅስቃሴ ለመግታት በከተማችንም ማህበራዊና የንግድ ተቋማትን ለማስጓጎል የተሞከረ ቢሆንም በአስተዋዩና ሰላም ወዳዱ የከተማችን ነዋሪዎች ሰላማዊ እንቅስቃሴዎች እንደቀጠሉ ናቸው ሲል ቢሮ ገልጿል። ከባህርዳር ከተማ የሚነሱ እና ወደ ተለያዩ የክልሉ ከተሞች የሚደረጉ የትራንስፖርት አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን ያስታወቀው ቢሮው በከተማው የባስ፣ የታክሲና የባጃጅ እንቅስቃሴ በተለመደው አግባብ ህብረተሰቡን እያገለገሉ ነው ብሏል።
በዛሬው እለት የቆቦ ከተማ ወደ መደበኛ ህይወቷ መመለሷን እና የሚታየው ሁሉ የበአል ድባብ መሆኑን ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የከተማዋ ነዋሪ ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጸዋል። ከተማዋ ትላንት ሰላሟ ተመልሶ ነበር አሁን ደግሞ ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ ያለው ድባብ የበአል ነው ሲሉ ተናግረዋል።
በደብረብርሃንም ሰላማዊ እንቅስቃሴ መኖሩን የገለጹልን የከተማዋ ነዋሪ የትራንስፖርት አገልግሎት መኖሩን እና የንግድ እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውንም አመላክተዋል። ከአዲስ አበባ የሚመጡ እና ወደ አዲስ አበባ የሚሄዱ መኪኖች ሲያልፉ መመልከታቸውንም አስታውቀዋል።
በተጨማሪም በሰሜን ወሎ ዞን አካባቢ ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ የፋኖ አባላት የመንግሥትን የሰላም ጥሪ በመቀበልና ይፋዊ ይቅርታ በማቅረብ ወደ መደበኛ ህይወታቸው ለመመለስ መስማማታቸውን የክልሉ መገናኛ ብዙሃን አስታውቀዋል። የፋኖ አባላቱ ይፋዊ ይቅርታ በመጠየቅ የመንግሥትን የሰላም ጥሪ መቀበላቸውን በማሳወቅ ከክልሉ መንግሥት እና ከመከላከያ ሠራዊት አመራሮች ጋር ውይይት አድርገው ወደ መደበኛ ህይወት ለመመለስ መስማማታቸውን የክልሉ መንግሥት አስታውቋል ሲሉ ዘገባዎቹ አካተዋል።
የክልል ልዩ ኃይል አባላትን ወደ ሌሎች የጸጥታ መዋቅሮች የማስገባት ፕሮግራም በመላ ሀገሪቱ የሚተገበር መሆኑን እና ሥራውም በሁሉም ክልሎች በተመሳሳይ ጊዜ እየተካሄደ እንደሚገኝ መንግስት ማስታወቁን መዘገባችን ይታወሳል። ሆኖም በአማራ ክልል በሚገኙ የተወሰኑ የልዩ ኃይል ክፍሎች ውስጥ፤ በአንድ በኩል የመልሶ ማደራጀት ሥራውንና ዓላማውን በአግባቡ ባለመረዳት፤ በሌላ በኩል የጥፋት አጀንዳ አራጋቢዎች ሆን ብለው በሚነዙት የሐሰት ወሬ በመጠለፍ ሂደቱን የሚያውኩ ተግባራት ታይተዋል ማለቱም ተመላክቷል።
ፌደራል መንግሥት የክልል ልዩ ኃይሎችን መልሶ ለማደራጀት የሚያደርገውን እንቅስቃሴ በመቃወም የአማራ ክልል ዋና ከተማ ባህርዳርን ጨምሮ በበርካታ የክልሉ ከተሞች ተቃውሞዎች መካሄዳቸውን የተመለከተ ዘገባ ማቅረባችን ይታወሳል። በክልሉ የሚገኙ አንዳንድ ከተሞች ጥብቅ ክልከላዎችን ማስተላለፋቸውም ተካቷል።
ልዩ ሃይሉን መልሰን የምናደራጅበት ምክንያት ተጨማሪ ብቃት ያለው ሃይል ለመገንባት መሆኑን በወጉ ባላማስገንዘባችን ነው ህዝቡ ስጋት ያደረበት ሲሉ የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ አባልና የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ግርማ የሽጥላ መግለጻቸውንም መዘገባችን ይታወቃል። አስ