ዜና፡ የአማራ ክልል ዋና ከተማ ባህርዳርን ጨምሮ በበርካታ የክልሉ ከተሞች ዛሬም ተቃውሞዎች ተካሂደዋል፤ በአንዳንድ ከተሞች ጥብቅ ክልከላዎች ተጥለዋል

ፎቶ ከማህበራዊ ሚዲያ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 3/2015 ዓ.ም፡- ፌደራል መንግሥት የክልል ልዩ ኃይሎችን መልሶ ለማደራጀት የሚያደርገውን እንቅስቃሴ በመቃወም የአማራ ክልል ዋና ከተማ ባህርዳርን ጨምሮ በበርካታ የክልሉ ከተሞች ዛሬም ተቃውሞዎች መካሄዳቸው ተገለጸ። አዲስ ስታንዳርድ በባህርዳር፣ ኮምቦልቻ እና ደብረብርሃን ተቃውሞዎቹ መካሄዳቸውን አረጋግጣለች። በክልሉ የሚገኙ አንዳንድ ከተሞች ጥብቅ ክልከላዎችን ማስተላለፋቸውም ተገልጿል።

በትላንትናው እለት በጎንደር ከተማ የተካሄዱ ተቃውሞዎችን ተከትሎ የከተማው አስተዳደር የፀጥታ ኮማንድ ፖስት የከተማዉን ሰላምና የህግ የበላይነት ለማረጋገጥ እንዲቻል ክልከላዎችን መጣሉ ተዘግቦ ነበር። ከተፈቀደለት የመንግስት የፀጥታ ኃይል ውጭ የጦር መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስ እና መቶከስ፣ ድምፅ አልባና ስለታማ የሆኑ መሳሪያዎችን ይዞ መንቀሳቀስ በክልከላው መካተታቸውም ተመላክቷል።

ከጎንደር ከተማ በተጨማሪ በደብረ ብርሃን፣ ደሴ እና ወልድያ፣ በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሄረሰብ ዞን አስተዳደር ተመሳሳይ ክልከላዎች መጣላቸው ታውቋል።

በዛሬው ዕለት በክልሉ ከተካሄዱ ሰልፎች መካከል በባህር ዳር እና በደብረ ብርሃን ከተሞች እረብሻ፣ የተኩስ ድምጽ እና የንብረት ቃጠሎዎች እንደነበሩ ነዋሪዎች ለአዲስ ስታንዳርድ አረጋግጠዋል። ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ የደብረብርሃን ከተማ ነዋሪ ለአዲስ ስታንዳርድ እንዳስታወቁት ከንጋት ጀምሮ እስከ ቀትር ድረስ ከፍተኛ የተኩስ ድምጽ በከተማዋ መኖሩን ገልጸው በተኩሱም የቆሶሉ እና የሞቱ መኖራቸውን አረጋግጠዋል፤ የሟቾቹን ቁጥር ለመናገር ሁኔታው አያመችም አሁንም ከተማዋ አልተረጋጋችም ሲሉ ገልጸዋል።

በተመሳሳይ በኮምቦልቻ ከተማ በተካሄደው ተቃውሞ ንጹሃን ነዋሪዎች መሞታቸውም ተጠቁሟል። አዲስ ስታንዳርድ የሟቾቹን ቁጥር ለማረጋገጥ ያደረገችው ጥረት አልተሳካም።

በሌላ በኩል ሳምንት ባልሞላ ግዜ ውስጥ አምስተኛ መግለጫውን ያወጣው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ አብን የገዢው ፓርቲ ብልጽግና የክልል ልዩ ኃይሎችን መልሶ ለማደራጀት በሚል ያስተላለፈውን ውሳኔውን እንዲያጥፍ ጠይቋል። የገዥው ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ውሳኔ በሁሉም ክልሎች ልዩ ኃይሎች ላይ በእኩል ደረጃ ተፈጻሚ የማይሆን እና የውሳኔው ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ የአማራ ልዩ ኃይልን ትጥቅ ማስፈታት ነው ሲል በድጋሚ ኮንኗል

ገዥው ፓርቲ የአማራ ክልል ልዩ ኃይልን ለማፍረስ ያሳለፈውን ውሳኔ እና ውሳኔውን ለማስፈጸም እየሄደበት ያለው መንገድ በአሁኑ ሰዓት በአማራ ክልል የተከሰተውን አለመረጋጋት እና የጸጥታ መደፍረስ ያስከተለ እና ሕዝባችንን ለጥቃት፣ ክልሉን ለከፍተኛ አለመረጋጋት እና የሰላም እጦት የዳረገ ነው ሲል ገልጿል።

የፌደራል መንግስት እና የአማራ ክልል መንግስት የክልሉ ሕዝብ አደባባይ ወጥቶ ያቀረበውን ጥያቄ እንዲያከብሩ እና ድርጅታችን አብን ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ያቀረባቸውን ጥሪዎች እና የውሳኔ ሃሳቦች ተቀብለው ሥራ ላይ እንዲያውሉ ሲል ጥሪውን በድጋሚ አስተላልፏል፡፡ አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.