ዜና፡ መንግስት ሜድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በለገደንቢ የሚያከናውነው የወርቅ ማውጣት ስራ ፈቃድ እንዲያቋርጥ ሂዩማን ራይት ዎች ጠየቀ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 18/2015 ዓ.ም፡- ሜድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በለገደንቢ የሚያከናውነው የወርቅ ማውጣት ስራ ፈቃድ እንዲያቋርጥ ሂዩማን ራይት ዎች ባወጣው መግለጫ የኢትዮጵያ መንግስትን ጠየቀ።

ሂዩማን ራይት ዎች ዛሬ ባወጣው መግለጫ በለገደንቢ የወርቅ ማውጣት ስራ በማከናወን ላይ የሚገኘው የሜድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ፣ የወርቅ ምርቱ በዋነኝነት ከለገደንቢ የሆነው የስዊሱ የማጣሪያ ኩባንያ አርጎር ሄሮውስ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን የሚቀርቡ በማህበረሰቡ የሚደርሰውን ጉዳቶች ላይ የሚያጠነጥኑ ዘገባዎችን ችላ ማለታቸውን ኮንኗል። ኩባንያዎቹ ውጤታማ የሆነ ብክለት የሚቀንስ እርምጃ እስኪወስዱ ድረስ መንግስት ፈቃዳቸውን እንዲያቋርጥ ጠይቋል።

ለበርካታ አመታት በለገደንቢ የሚካሄደው የወርቅ ማምረት ስራ በአከባቢው ማህበረሰብ ዘንድ ከፍተኛ የሆነ የጤና ጉዳት እያስከተለ መሆኑን የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ማስታወቃቸውን መግለጫው አውስቷል።

የለገደንቢ የወርቅ ማምረት ስራ በወቅቱ የነበረውን ተቃውሞ ተከትሎ በግንቦት ወር በ2010 ዓ.ም እንዲቋረጥ መደረጉ ያወሳው የሂዩማን ራይት ወች መግለጫ ዋነኛው ምክንያት ደግሞ በወርቅ ምርቱ ወቅት የሚደርሰው ብክለት ለአከባቢው ማህበረሰብ አስጊ አለመሆኑ እስኪረጋገጥ በሚል ነበር አመላክቷል።

ሜድሮክ በለገደንቢ በድጋሚ የማምረት ስራ ከኢትዮጵያ መንግስት አግኝቶ እየሰራ መሆኑ የጠቆመው መግለጫው ነገር ግን ብክለት ለመቀነስ ምን አይነት እርምጃ እንደሚወሰድ የተገለጸ ነገር አለመኖሩን አስታውቋል።

ሂዩማን ራይት ወች ባደረገው ጥናት ከሁለት አመት በፊት እንደገና ወርቅ ማምረት የጀመረው ኩባንያው ብክለቱን ለመቀነስ ምንም አይነት ስራ አልሰራም ብሏል። ምንም አይነት ማሻሻያ እርምጃ ሳይወስድ መንግስት ለኩባንያው ስራ እንዲጀምር መፍቀዱ የህጻናት እና ጎልማሶች በጤንነት የማስጠበቅ መብትን የጣሰ ነው ሲል ገልጿል።

የኢትዮጵያ መንግስት፣ ሜድሮክ እና አርጎር ሄሮውስ የአለም አቀፍ የከባቢ አየርንብረት እና የጤና ባለሞያዎች ምክረ ሀሳብ እና መመሪያን በመከተል ሁሉን አቀፍ የሆነ ሂደት መከተል እንደሚኖርበትም ጠቁሟል። በለገደምቢ የወርቅ ማውጫ አከባቢ የሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎችም ተገቢ ካሳ እንዲፈጸምላቸው አሳስቧል።

ደረጃውን የጠበቀ ዲዛይን፣ በአፈሩ እና ውሃው ላይ የሚኖረው ጎጂ የኬሚካል መጠን አለም አቀፍ ደረጃን ባልበለጠ መሆኑ እስኪረጋገጥ ድረስ መንግስት በለገደንቢ ወርቅ እንዲያወጣ ለሜድሮክ ኩባንያ የሰጠው ፈቃድ እንዲያቋርጥ። ሜድሮክ ኩባንያ እና አርጎር ሄሮውስ ኩባንያ በይፋ ስላካሄዱት ማስተካከያ እና ስለፈጸሙት ካሳ ለህዝብ እንዲያሳውቁ ጠይቋል።

በኦሮምያ ክልላዊ መንግስት እና በሜድሮክመካከል የተደረሰውን መግባቢያ ሰነድ የፌደራል መንግስቱ ይፋ እንዲያደርግም አሳስቧል። አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.