ዜና፡ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የአውሮፓ ህብረት ምክር ቤት ያሳለፈውን ውሳኔ በበጎ ጎኑ እንደሚያየው አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 19/2015 ዓ.ም፡- የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የአውሮፓ ህብረት ምክር ቤት ኢትዮጵያን አስመልክቶ ያሳለፈውን ውሳኔ የተመለከተ መግለጫ አውጥቷል። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በመግለጫው የምክር ቤቱ ውሳኔን በበጎ አይኑ እንደሚያየውም አስታውቋል። መግለጫው አያይዞም ምክር ቤቱ በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ትግበራ ላይ የተገኙ ውጤቶችን እውቅና መስጠቱን ገልጿል። ኢትዮጵያ ከህብረቱ ጋር ያላትን ትብብር እንደገና ለማደስ አበክራ እየሰራች እንደምትገኝም ያስታወቀው መግለጫው የህብረቱ ምክር ቤት ያሳለፈው ውሳኔ ትብብሩን ይበለጥ ለማጠናከር እንደሚያግዝ ጠቁሟል።

ህብረቱ ባሳለፈው ውሳኔ  አመታዊ የባለብዙ ዘርፍ የድጋፍ ፕሮግራም እንደገና ለማስጀመር ዝግጁ መሆኑን፣ አለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ሀገሪቱ የጀመረችውን የኢኮኖሚ ማረጋጋት እና ማሻሻያ አጀንዳ ይበልጥ እንዲያበረታቷት መጠየቁ፣   አበዳሪ ሀገራት የሚያከናውኑት የኢትዮጵያን ዕዳ የማሸጋሸግ የድርድር ሂደት በአፋጣኝ እንዲቋጩ መጠየቁን በመልካም ጎኑ እንደሚቀበለው በመግለጫው አመላክቷል።

የአውሮፓ ህብረት ምክር ሚያዚያ 16 ቀን 2015 ባወጣው መግለጫ ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ግንኙነት ሙሉ ለሙሉ ለማደስ እና ሀገሪቱን ለማገዝ እንዲሁም ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ለማስቻል የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማበርከት ዝግጁ መሆኑን አስታውቆ ግንኙነቱን ሙሉ ለሙሉ ለማደስ ቅድመ ሁኔታ ማስቀመጡን፤ ቅድመ ሁኔታውም የፌደራል መንግስቱ ከትግራይ ሀይሎች ጋር የደረሱት ስምምነት በዘላቂነት ተተግብሮ ካየሁት ብቻ ነው ማለቱን መዘገባችን ይታወሳል።

ኢትዮጵያ ሰላሟን ለማስጠበቅ ከፍተኛ ጥረት እያደረገች በመሆኗ፣ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ማድረጓ፣ በጦርነቱ ሳቢያ የተጎዱ ዜጎቿን ለማቋቋም እየጣረች ስለምትገኝ ወዳጆቿ የሆኑ ሀገራት ግንኙነታቸውን ለማጠናከር እየሰሩ መሆናቸውን መግለጫው አትቷል። አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.