አዲስ አበባ፣ ህዳር 23/2015 ዓ.ም፡- ሀብት በማስመዝገብና በማሳወቅ ሂደት ፤ አመራሮችንና ባለሙያዎች ሳያስመዘገቡ የቀሩትን ሀብት የጠቆመ ዜጋ ከተጠቆመው ሀብት 25 በመቶ እንዲያገኝ እንደሚደረግ የፌደራል ስነምግባር እና ፀረ ሙስና ኮሚሽን አስታውቋል።
ለዚህም ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝና ይህም በአዋጅ ቁጥር 668/2002 በግልፅ መስፈሩን በፌደራል ስነምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን የሙስና መረጃ አስተዳደሥ መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ፈርዳ ገመዳ ገልጸዋል።
ኮሚሽኑ እስካሁን 763 የመንግስት አመራሮችን ቢለይም፤ እስካሁን ሀብታቸውን ያስመዘገቡት 20 በመቶው ብቻ መሆናቸው ተጠቅሷል። ከዚህ ውስጥ 107ቱ በማንዋል 42ቱ በኦንላይን ምዝገባ ስርዓት ያከናወኑ መሆናቸው ተገልጿል።
ኮሚሽኑ ከFM 97.1 ጋር በነበረው ቆይታ ሀብታቸውን ያላስመዘገቡ ሰዎች በህግ ፊት ተጠያቂ ከመሆናቸው በፊት ሀብታቸውን እንዲያስመዘግቡ ጥሪውን አቅርቧል። አክሎም እስካሁን 2 ሺህ 272 የፌደራል ተቋማት፣ መካከለኛ አመራሮችና ባለሙያዎች ሀብታቸውን ማስመዝገባቸውን ጠቅሷል።
በኦንላይን ምዝገባ ስርዓቱ ላይ አልፎ አልፎ የሲስተም ችግር መኖሩን የጠቀሰው ኮሚሽኑ፤ ችግሩን ለመፍታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየሰራሁ ነው ብሏል።