ዜና፡ ከዚህ ዓመት ጀምሮ የዩኒቨርስቲ መውጫ ፈተና በኦንላይን ለመስጠት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ህዳር 22/ 2015 ዓ.ም፡- ከዚህ ዓመት ጀምሮ  የዩኒቨርስቲ መውጫ ፈተና በሁሉም መደበኛና መደበኛ ባልሆኑ መርሀግብሮች የሚመረቁ ተማሪዎችን እንደሚመለከትና ፈተናውን በኦንላይን ለመስጠት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ ገልፁ። 

የዩኒቨርስቲ መውጫ ፈተና ከመደበኛ ተማሪዎች ባሻገር የማታና የርቀት ተመራቂ ተማሪዎችን እንደሚመለከት የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል።

የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) በመውጫ ፈተና ዙሪያ ለመንግስትና ለግል ዩኒቨርስቲዎች የተዘጋጀ የምክክር መድረክ ሲከፍቱ እንዳሉት መውጫ ፈተና በሁሉም ዩኒቨርስቲዎች ለሚማሩ የቀን ፣የማታና የርቀት መርሀ ግብር ተመራቂዎች ይሰጣል።

በመንግስትና የግል ዩኒቨርስቲዎች ተግባራዊ የሚደረገውን የመውጫ ፈተና በኦንላይን ለመስጠት በመታቀዱ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ የመሠረተ ልማት አቅሞቻቸውን ከወዲሁ በማረጋገጥ ለፈተናው ተገቢውን ዝግጅት እንዲያደርጉ ሚኒስትር ዴኤታው አሳስበዋል።

የከፍተኛ ትምህርት አካዳሚክ ጉዳዮች መሪ ስራ አስፈጻሚ ኤባ ሚጀና (ዶ/ር ) የመውጫ ፈተና የትምህርት ጥራትን ከማስጠበቅ ባሻገር የተማሪዎችንና የተቋማቱን ብቃት ለማሳደግ እንደሚያስችል ጠቁመዋል።

በምክክር መድረኩም በመውጫ ፈተና ዙሪያ እየተደረገ ያለው ቅድመ ዝግጅት ፣ የመሠረተ ልማትና የ2015 ምሩቃን መረጃዎች ቀርበው ውይይት መደረጉን ከትምህርት ሚንስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.