አዲስ አበባ፣ የካቲት 10/2015 ዓ.ም፡- የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የካቲት 8 ቀን 2015 ዓ.ም. በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ ቦታዎች የቧንቧ ውሃ አቅርቦት ከወር በላይ ለሆነ ጊዜ መቋረጡን ተከትሎ ላጋጠማቸው የውሃ ችግር መንግሥት መፍትሔ እንዲሰጣቸው ጥያቄ ለማቅረብ ሰልፍ በወጡ ነዋሪዎች ላይ በፖሊስ በተወሰደ የኃይል እርምጃ “ሦስት ሰዎች ጭንቅላታቸውና ደረታቸው ላይ በጥይት ተመተው የተገደሉ ሲሆን ቢያንስ በ30 ሰዎች ላይ የተለያየ መጠን ያለው የአካል ጉዳት” መድረሱን ዛሬ ባወጣው መግለጫ ገለጸ።
“ኢሰመኮ የዐይን ምስክሮችን፣ ተጎጂዎችን፣ የተጎጂ ቤተሰቦችን እና የጤና ባለሙያዎችን በማነጋገር ባሰባሰበው መረጃ እና ማስረጃ መሠረት 3 ሰዎች ጭንቅላታቸውና ደረታቸው ላይ በጥይት ተመተው የተገደሉ ሲሆን ቢያንስ በ30 ሰዎች ላይ የተለያየ መጠን ያለው የአካል ጉዳት መድረሱን አረጋግጧል” ብሏል፡፡
ነገር ግን በትላንትናው እለት የከተማዋ ነዋሪዎች ለአዲስ ስታንዳርድ እንደነገሩት ለአመታት በውሃ እጠረት ሲቸገር የነበረ የከተማዋ ነዋሪ ችግሩ እንዲቀረፍ ጄሪካን ይዘው ሰላማዊ ሰላፍ በመውጣታቸው ብቻ በልዩ ሀይል ተኩስ ተከፍቶባቸው 6 ሰው የተገደሉ ሲሆን 15 ሰው ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሰዋል ብለዋል። በህክምና ላይ ያሉት በአስጊ ሁኔታ ውስጥ በመሆናቸው የሟቹቹ ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል ገልጸው ነበር።
ኢሰመኮ እንዳለው የአካባቢው ባለሥልጣናት በበኩላቸው ለደረሰው ጉዳት ምክንያት የሆነው ከሰልፈኞች ውስጥ የተወሰኑት ሰዎች የከተማው የውሃ አገልግሎት ጽሕፈት ቤት ላይ ድንጋይ መወርወራቸውን እና የመኪና መንገድ መዝጋታቸውን ተከትሎ በክልሉ ፖሊስ በተወሰደ የኃይል እርምጃ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ የተወሰደው የኃይል እርምጃ ከነገሩ ሁኔታ አንጻር ሲታይ ተመጣጣኝ ያልሆነ መሆኑን ገልጸው “አንገብጋቢ በሆነ የውሃ አቅርቦት ጥያቄ ሰልፍ ወጥተው ድንጋይ በወረወሩና መንገድ በዘጉ ሰዎች ላይ ሕይወት የሚያጠፋ መሣሪያ ተጠቅሞና ጥይት ተተኩሶ ነዋሪዎች መገደላቸው ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለው እርምጃ በመሆኑ የክልሉ መንግሥት አስቸኳይ ማጣራት አድርጎ በአጥፊዎች ላይ ተጠያቂነት ሊረጋገጥ እና የተጎዱ ሰዎችም ተገቢውን ካሳ ሊያገኙ ይገባል” ብለዋል፡፡ ዋና ኮሚሽነሩ አክለውም ለወደፊቱም ተመሳሳይ ዓይነት የመብት ጥሰቶች እንዳይፈጸሙ ለጸጥታ ኃይሎች ግልጽ አመራር እንዲተላለፍ ያስፈልጋል በማለት አሳስበዋል፡፡
የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ጉዳዩን አስመልክቶ በዛሬው ዕለት ባወጣው የሃዘን መግለጫ በበኩሉ ከትላንትና በከተማዋ በሰዎች ሕይወት ላይ በደረሰው ጉዳት ከልብ ማዘኑን ገልጿል።
“ድርጊቱ ልብ የሚሰብርና አሳዛኝ ክስተት ነው። መሆን ያልነበረበት ነገር ደርሷል“ ያለው የከተማ አስተዳደሩ፤ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት የደረሰው ጉዳት አስፈላጊው ማጣራት በገለልተኛ አካል እንዲካሄድ የበኩሉን ጥረት እንደሚያደርግም አስታውቋል። አስ